ተከታታይ ግንዛቤ ማስጨበጫ - ክፍል 6
የመፍትሄ አቅጣጫዎቻችን ምን ምን ናቸው? (ባለቀጣይ ክፍል)
ማክሰኞ ሚያዝያ 18/2008

የትግላችን መነሻ የሆነውን ብሄራዊ ጭቆና መገለጫዎች በተከታታይ 4 ክፍሎች በወጡ የግንዛቤ ማስጨበጫዎች ስንመለከት የቆየን መሆኑ ይታወሳል፡፡ በመቀጠልም የጭቆናውን ይዘት እና የመፈፀም አቅማችንን ግምት ውስጥ ያስገቡ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን መዘርዘር የጀመርን ሲሆን ከዚህም ውስጥ ክፍል አንድን ባለፈው አቅርበናል፡፡ ዛሬ ደግሞ በክፍል ሁለት የመፍትሄ ጥቆማችን ተጨማሪ ነጥቦችን የምንዳስስ ይሆናል - ኢንሻአላህ!

ጥያቄ 2 - የመፍትሄ አቅጣጫዎቻችን ምን ምን ናቸው? (ባለቀጣይ ክፍል)

3/ በኢኮኖሚው እና ልማት ዘርፍ መንቀሳቀስ፤

መንግስት ሙስሊሙን ህብረተሰብ ለማዳከም ሲሸርብ የቆየውን ሴራ በቅጡ ከሚያስገነዝቡ ነገሮች አንዱ ሙስሊሙ በአገሪቱ የኢኮኖሚ እና የልማት ስራዎች ላይ ያለው ተሳታፊነት እንዲገደብ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱ ነው፡፡ ህዝበ ሙስሊሙ እንደአንድ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የህብረተሰብ ክፍል (ኮሚውኒቲ) የራሱ የሆኑ የፋይናንስ እና የኢንቨስትመንት ተቋማት በማደራጀት የራሱን ህይወት አሻሽሎ አገሩን እና ወገኑንም መጥቀም የሚችልበትን እድል ተነፍጓል፡፡ ወደተሻለ የኢኮኖሚ አቅም እና የተደራጀ እንቅስቃሴ የሚያደርሱት በሮች ሁሉ ተዘግተውበታል። ሃይማኖታዊ ማንነቱን ከግምት ያስገቡ የፋይናንስ ድጋፍ አማራጮችን እንዳይጠቀም በተለያዩ አዋጆች እና መመሪያዎች እቀባ የተደረገበት ሲሆን ይህም ለሙስሊሙ ጭቆና፣ ለአገሪቱም በደል መሆኑ አያጠራጥርም፡፡

ይህን ኢ-ፍትሀዊ በደል ለመቅረፍ ሕዝበ ሙስሊሙ የመንግስትን የመጨቆኛ መሳሪያዎች በትግሉ ተሻግሮ በማለፍ በኢኮኖሚውም ይሁን አገሩን በማልማት ስራ ሂደቱ ውስጥ ተሳታፊነቱን የሚያጎሉ እርምጃዎችን ሊወስድ ይገባል፡፡ ሊያስገልሉት የሚፈልጉ አካላትን ጫና በመቋቋምም በፋይናንስ ራሱን ለማሳደግ እንቅስቃሴ ማድረጉ ከመፍትሄው አቅጣጫዎች ውስጥ አንዱ መሆኑ በጥብቅ ሊሰመርበት ይገባል፡፡

4/ ራስን ማደራጀት፤

አምባገነን ስርዓቶች ዜጎቻቸውን አንገት አስደፍተው ለመጨቆን ከሚወስዷቸው የተለያዩ እርምጃዎች መካከል የገዛ ዜጎቻቸውን ድርጅት አልባ ማድረግ አንዱ ነው። ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ላይም ገና ከጠዋቱ የተተገበረው ይኸው ነበር። የተደራጀ እንቅስቃሴ የህዝብ የመብት ጥያቄዎች ለመፍትሄ አቅራቢው አካል የሚደርሱበትን እና መቋጫ የሚያገኙበትን ጤናማ አሰራር የሚፈጥር እንደመሆኑ በተለይ እንደአገራችን ባሉ ዲሞክራሲ ያልዳበረባቸው አገራት የሚጫወተው ሚና ቀላል አይደለም፡፡ ድርጅታዊ እንቅስቃሴም የአንድ አገር ሲቪል ማህበረሰብ ጤናማ እድገት የሚያሳይበት ትልቅ ዘርፍ ነው፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ግን አምባገነን መንግስታት ምንጊዜም መደራጀትን እንደስጋት አድርገው ለማሳየት ሲጥሩ ይታያል፡፡ ከዚያም አልፈው እንደስልጣን ማራዘሚያ እና በዜጎች መካከል ስጋት እና ጥርጣሬ የመፍጠሪያ መንገድ አድርገው ዘወትር ይጠቀሙበታል፡፡

የትግላችን መነሻ ከሆኑት ሶስት ጥያቄዎች መካከል ሁለቱ ጥያቄዎች ከመደራጀት እና ከድርጅታዊ ህልውና ጋር የተያያዙ ነበሩ፡፡ አምባገነኑ ስርዓት ሙስሊሙ ህብረተሰብ በነጻ እንዲደራጅ እድሉን ለመስጠት ባይፈልግም ይህ ግን ራሳችንን ከማደራጀት ስራ ሊያግደን አይገባም። ብሄራዊ ጭቆናን ለማስወገድም ይሁን ቀጣይነት ያለው መብት የማስከበር እንቅስቃሴ ለማድረግ መደራጀት በእርግጥም ወሳኝ ነውና የመደራጀት እና የማደራጀት ስራ ፊት ለፊታችን እንደሚጠብቀን አውቀን እንደመፍትሄ አቅጣጫ ልንይዘው ይገባል።

*********
ካሁን ቀደም የወጡትን የግንዛቤ መፍጠሪያ መልእክቶች ለማንበብ በሚከተሉት ሊንኮች ይጠቀሙ፡-

ተከታታይ ግንዛቤ ማስጨበጫ - ክፍል 1፡- https://goo.gl/MpQxxc 
ተከታታይ ግንዛቤ ማስጨበጫ - ክፍል 2፡- https://goo.gl/SKbBAa 
ተከታታይ ግንዛቤ ማስጨበጫ - ክፍል 3፡- https://goo.gl/6pjF4n 
ተከታታይ ግንዛቤ ማስጨበጫ - ክፍል 4፡- https://goo.gl/z7GTML 
ተከታታይ ግንዛቤ ማስጨበጫ - ክፍል 5፡- https://goo.gl/9ON2gr 
*********

ትግላችን በተጠናከረ መልኩ ሁሉን አሳታፊ ሆኖ ይቀጥላል!
ለመንግስት እና ለአህባሽ ሴራ አንበገርም!
ብሄራዊ ጭቆናን አንሽከምም!
ትግላችን እስከድል ደጃፎች በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል!
ድምጻችን ይሰማል!
አላሁ አክበር!