ሐምሌ 27 

ረቡእ ሐምሌ 27/2008

በኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች የትግል ሂደት ውስጥ ወርሃ ሐምሌ ልዩ ቦታን ይዞ የሚገኝ ወር ነው። የአገሪቱን ህጎች ጠብቆ እና አስጠብቆ ሰላማዊ በሆነ ልዩ ስርዓት ፍትህን ለማግኘት ድፍጹን ከፍ በማድረግ ‹‹ድምጻችን ይሰማ›› የሚል ጥሪ ባደረገ ህዝብ ላይ የጥቁር ሽብር የታወጀበት እና የተፈጸመበት ወር ብቻ ሳይሆን ይህን የፍትህ ፈላጊነት መርሁን ሳይለቅ ጥያቄዎቹ እስከሚመለሱበት ቀን ድረስ ትግሉን እንደሚቀጥል ቃል የተጋባበት ወር ነው። ሙስሊሙ ህብተሰብ በገባው ቃል መሰረት ትግሉን በመቀጠል በአምባገነኑ ስርዓት የስለላ፣ የፓሊስ እና የወታደራዊ ሃይል ኢሰብዓዊ እርምጃ የደረሰበትን በደል እና ግፍ በፍርድ ቤት መድረክም ዳግም እውን ለማድረግ ከሁለት ዓመታት በላይ የቆየ ግብግብ ያደረገ ሲሆን በዚህ ትግል መካከል ፍትህ በአገሪቱ መቀበሯ እውን የሆነበትን ሐምሌ 27ን እናገኛለን።

አዎ! ሐምሌ 27 በኢትዮጵያዊያን፣ በተለይም ደግሞ በሙስሊሙ ማህበረሰብ ዘንድ የማትረሳ እለት ሆና አልፋለች - የሰላም መልእክተኞች ላይ የአሸባሪነት ታፔላ የተለጠፈባት እለት! ኢትዮጵያዊው ሙስሊም ማህበረሰብ መፍትሄ ያፈላልጉለት ዘንድ ፈርሞ በላካቸው ንጹሃን ሙስሊሞች ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፏል፡፡ እኒህ ሙስሊም ግለሰቦች ከቀድሞውም የሚታወቁት መልካምን በመስራት፣ ሌሎችን በመርዳት እና በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል መከባበርን፣ መተሳሰብን እና መደጋገፍን በመስበክ ነበር፡፡ ራሳቸውን የስብከታቸው ምልክት በማድረግም መታወቅ ችለው ነበር፡፡ ግና ፍትሃዊ ሳይሆን ፓለቲካዊ እና አምባገነናዊ ውሳኔ በተላለፈባት በዚያች ‹‹ሐምሌ 27›› ግን እኒያ የሰላም አምባሳደሮች ‹‹ሽብርተኞች ናችሁ›› ተባሉ፡፡ በኢትዮጵያ ምድር በችሎት አዳራሽ ውስጥ ፍትህ በግላጭ ተቀበረች!

ሐምሌ 27 መንግስት ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞችን በጭቆናው ቀንበር ስር ለማድረግ የማይፈነቅለው ድንጋይ እንደሌለ እና በስሩ ያሉትን ሁሉ ከመጠቀም እንደማይመለስ ግልስ ያደረገባት እለት ብትሆንም ለሙስሊሙ ህብረተሰብ ግን በትግሉ ጸንቶ የቆመባት እና ቀጣይ የትግል ሂደቱ ከሚከፍለው መስዋእትነት ጋር የሚጣጣም መሆን እንዳለበት የመጨረሻ ውሳኔ ላይ የደረሰባት እለትም ነበረች። ከዚህ አንጻር በዚሁ ወር ውስጥ የደረሱ የተለያዩ የግፍ እርምጃዎችን ሳንዘንጋ ‹‹ሐምሌ 27 ለመብታችን መከበርና ለእምነት ነጻነታችን እስከመጨረሻው ለመታገል የገባነውን ቃል ኪዳን ማደሻ እለት ነው›› ብንል በእርግጥም አልተሳሳትንም፡፡ በእርግጥም በታሪክ ብሩህ ቀለማት ተጽፈው ከተቀመጡ በርካታ አረመኔያዊ እርምጃዎች መካከል ሆናም እንኳ የድል አድራጊነታችን ብርሃን የፈነጠቀባት፣ ፍትህ በተቀበረበት መድረክ ፊት ለፊት ላይ ሆነን የትግል ጽናታችን ውጤት የሚሆነውን ዘላቂ ነጻነት ያሸተትንባት ቀን መሆኗ ሊዘነጋ አይችልም።

ሐምሌ 27 አንገታችንን የምንደፋባት ሳትሆን አንገታችን እንዲደፋ ለሚባክነው ስርዓት ‹‹እምቢየው›› የምንልባት ቀንም ናት። ፍትህ እና ነጻነት መስዋእትነትን ተክትለው የሚመጡ እንጂ በችሮታ የሚሰጡ አለመሆናቸውንም በመረዳት ዓላማችንን እስከምናሳካ ድረድ ከመታገል ውጭ አማራጭ የሌለን መሆኑን ልንረዳ ግድ ይለናል፡፡ የትግላችን ውጤት የሆነውን አንድነታችንን አጠናክረን እና ስርዓቱ እያወቅነውም ይሁን ሳናውቀው ለእኛ መከፋፋያ እንዲሆኑ የከፈታቸውን የልዩነት በሮች በሙሉ በመዝጋት ትግላችን ባስቀመጠልን የትግል መርህ ውስጥ ራሳችንን አስገብተን ዘላቂ መብታችንን ለማስከበር የምናደርገውን ጉዞ አጠናክረን መቀጠል አለብን።

የተቀበረችው ፍትህ መገለጫ የሆኑት የሰላም አምባሳደሮቻችን እና በተመሳሳይ እርምጃ በአገሪቱ ውስጥ በእስር ቤት ሳይቀር የጭቆናውን ገፈት በቀዳሚነት እየቀመሱ ያሉ መሪዎቻችን እና እንቁዎቻችን ሐምሌ 27ን ሲያስቡ ኩራት የሚሰማቸው እንጂ በተበዳይነት ስሜት አንገታቸውን የሚደፉባት ቀን አይደለችም። ሙስሊሙ ህብረተሰብም የእነሱን ፈር በመከተል አንገቱን ቀና በማድረግ የተቀበረችው ፍትህ በአገራችን ዳግም እውን እስክትሆን በመታገል ዘላቂ መብቱን ለማስከበር በገባው ቃል መሰረት ጽኑነቱን ደጋግሞ የሚያውጅባት ቀን ሁና ትታሰባለች፤ ድልም ከአላህ እንጂ ከሌላ አይደለምና!

ሐምሌ 27 - ፍትህ በኢትዮጵያ የተቀበረባት፣ ለፍትህ ፈላጊው ሙስሊም የትግል ጽናት ግድ የሆነባት ቀን!
ትግላችን እስከድል ደጃፎች በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል!
ድምጻችን ይሰማል!
አላሁ አክበር!

Like ☑ Comment ☑ Share ☑