የወልዲያ ሰላም መስጂድ የጥበቃ ሰራተኞች ዋሃቢያ ናችሁ በሚል በአህባሽ መራሹ መጅሊስ ከስራ መባረራቸው ተዘገበ
ፍትህ ራዲዬ/ መጋቢት4/2009
۩○◙◙○◙◙○◙◙○◙◙○۩
በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን በወልዲያ ከተማ የሚገኘው ታላቁ የሰላም መስጂድ የጥበቃ ሰራተኞች ዋሃቢያ ናችሁ በሚል ከስራቸው መፈናቀላቸውን የፍትህ ራዲዬ ባልደረቦች ዘግበዋል፡፡
በወልዲያ ከተማ ከአወልያ ቀጥሎ ግዙፉ የሙስሊሙ ተቋም የነበረው  የወልዲያ መስጂዶች እና ትምህርት ቤቶች ማዕከል በመንግስት አስገዳጅነት ለአህባሾች እንዲሰጥ ከተደረገ በኋላ በስሩ ያሉትን ተቋሞች እያዳከሙት እንደሚገኙ የሚታወቅ ሲሆን ከተቋሙ ስር የነበረው የሰላም መስጂድንም ሙሉ ለሙሉ በአህባሾች ቁጥጥር ስር ለማድረግ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆናቸው ተዘግቧል፡፡
አህባሽ መራሹ የዞኑ እና የከተማው መጅሊሶች በተደጋጋሚ የመስጂዱን ኢማም ለመቀየር አቅደው ሳይሳካላቸው የቀረ ሲሆን በመስጂዱም በየአመቱ ረመዳን በመጣ ቁጥር አህባሾች ዳዕዋ እናደርጋለን በሚል ከኮምቦልቻ ከተማ እንደሚመጡ ይታወቃል፡፡
የመስጂዱን አስተዳደር  ከሙስሊሙ  ቢነጥቁም መስጂዱን በአህባሾች አስተምህሮ የተበከለ ለማድረግ  የሚያደርጉት ሙከራ እስካሁን ሊሳካ ባለመቻሉ ከመስጂዱ ጥበቃ ሰራተኞች በመጀመር ኸዲሞቹን እና ኢማሞቹን ከመስጂዱ ለማባረር እየተንቀሳቀሱ መሆናቸው ታውቋል፡፡
የወልዲያ ከተማ ህገ ወጡ መጅሊስ ሰብሳቢ በሆነው አቶ ሰይድ ኢድሪስ አማካኝነት ለረጅም አመታት የወልዲያ ሰላም መስጂድን በጥበቃ ሰራተኝነት ሲያገለግሉ የነበሩ 3 የጥበቃ ሰራተኞችን ዋሃቢያ ናችሁ በሚል ከስራቸው እንዲባረሩ ማስደረጉ ተዘግቧል፡፡
አቶ ሰኢድ የተባለው ቀንደኛ የአህባሽ ተላላኪ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን የወልዲያ ከተማ ሙስሊሞችን ሲያሳስር እና ሲያስደበድብ የነበረ ግለሰብ መሆኑ ይታወቃል፡፡
የአህባሽን አስተምህሮ አልተቀበላችሁም በሚል ዋሃቢያ የሚል ታፔላ በመለጠፍ ሶስቱን የመስጂዱን የጥበቃ ሰራተኞች እንዲባረሩ ያስደረገ ሲሆን ላለፉት ሁለት ወራትም ደሞዛቸው እንዳይከፈላቸው በማድረግ ከስራቸው ከ መጋቢት 1 ጀምሮ እንዲሰናበቱ ማድረጉ ተዘግቧል፡፡
ከመስጂዱ የጥበቃ ሰራተኝነት እንዲባረሩ የተደረጉት  አቶ  ቡሽራ አሰፋ፣አቶ ሙሀመድ አህመድ እና ሙሀመድ ሞላ መሆናቸው ታዉቋል፡፡
ሶስቱ የጥበቃ ሰራተኞች መስጂዱን በመንከባከብ እና ሃላፊነታቸውን በመወጣት ሁልጊዜም ትጉህ የነበሩ ሲሆን በስነ ምግባራቸው የአካባቢው ሙስሊም ሁሉ የሚመሰክርላቸው የነበሩ ትሁት ሰራተኞች እንደነበሩ ተዘግቧል፡፡
ህገ ወጡ የፌደራሉ መጅሊስ ባሳለፍነው አመት በባህርዳር ከተማ ባካሄደው ጉባኤ ላይ በአማራ ክልል የአህባሽ እንቅስቃሴ አስደሳች በሆነ ሁኔታ እየተስፋፋ መሆኑን በመግለፅ በወልዲያ ከተማ ብቻ የአህባሽ ዘመቻው እንቅፋት እንደተጋረጠበት መግለፁ ይታወሳል፡፡
የወልዲያ ሰላም መስጂድ በወሃብዬች ቁጥጥር ስር በመሆኑ ከሚመለከተው የመንግስት አካል ጋር በመነጋገር መስጂዱን ሙሉ ለሙሉ በአህባሾች እንዲመራ እና የአህባሽ አስተሳሰብ ብቻ በመስጂዱ እንዲሰጥ ጥረት እንዲደረግ ውሳኔ ላይ መድረሳቸው  ይታወቃል፡፡
ለወልዲያ መስጂድ ቀንደኛው የኮምቦልቻው አህባሽ ሙህዲንን ጨምሮ ሌሎች አህባሾች ተመድበው በመስጂዱ የተበከለ አስተምህሮታቸውን ለማሰራጨት  ከዚህ ቀደም ባደረጉት ሙከራ የመስጂዱ ጀምዓ ዳዕዋቸውን አቋርጦ ከመስጂዱ እንዲወጡ እንዳስደረጋቸው የሚታወስ ነው፡፡
የታላቁ የረመዳን ወር መምጣቱን ተከትሎ ሙስሊሙ በብዛት ወደመስጂዱ የሚመጣ በመሆኑ አህባሾች የተበከለ አስምህሮታቸውን በየመስጂዱ ለማሰራጨት ካሁኑ ቅድመ ዝግጅቶችን እና ይህን ለማድረግ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠርም የመስጂድ ጥበቆችን፣ኻዲሞችን እና ኢማሞችን ከቦታቸው ለማፈናቀል  ከወዲሁ እየተሰናዱ መሆናቸው ታውቋል፡፡ 

ተጨማሪ ምስል