የኢትዬጲያ ሁጃጆች የሚሳፈሩበት የኢትዬጲያ አየር መንገድ የናይጄሪያ ሁጃጆችን እያመላለሰ በመሆኑ የሚሳፈሩበት አየር መንገድ አጥተው በጅዳ ኤርፖርት እየተንገላቱ መሆኑ ታወቀ

ፍትህ ራዲዬ/መስከረም 20/2009

۩○◙◙○◙◙○◙◙○◙◙○۩

የዘንድሮውን ሃጅ ለማድረግ ወደ ሳኡዲ አረቢያ ያቀኑ ኢትዬጲያውያን ሃጃጆች ወደ ሃገራቸው ለመመለስ የሚሳፈሩበት አውሮፕላን በማጣታቸው በጅዳ ኤርፖርት እንግልት ላይ መሆናቸውን የፍትህ ራዲዬ ባልደረቦች ዘግበዋል፡፡

ህገ ወጡ የአህባሽ መጅሊስ በኢትዬጲያ ሃጃጆች ታሪክ ተከፍሎ የማያውቅ ክፍያ በዘንድሮ አመት ከእያንዳንዱ ሃጃጅ 70ሺህ ብር በመቀበል የሃጅ ጉዞ ማስደረጉ የሚታወቅ ሲሆን ሃጃጆች በኢትዬጲያ አየር መንገድ ትኬት የቆረጡ ቢሆንም በመመለሻቸው ቀን የኢትዬጲያ አየር መንገድ የናይጄሪያ እና የሌላ ሃገር ዜጎችን በማመላለስ ላይ በመጠመዱ ኢትዬጲያውያን ሃጃጆች በጅዳ ኤርፖርት ለሁለት ቀናት እንግልት ላይ መሆናቸው ታውቋል፡፡

ሁጃጆቹ በቆረጡት የአየር ትኬት መሰረት የበረራ ቀናቸው ሲቃረብ ህገ ወጡ መጅሊስ ከመካ ከተማ ወደ ጅዳ ኤርፖርት የወሰዷች ሲሆን በጅዳ ኤርፖርት ከደረሱ ቡኋላም የሚሄዱበት አውሮፕላን ሌሎች ሃጃጆችን እያመላለሰ በመሆኑ እነሱን ሊያስተናግዱ አለመቻሉ ታውቋል፡፡

በርካታ ቁጥር ያላቸው ሃጃጆች በጅዳ ኤርፖርት ላይ አሳፍሩን በማለት ሲጠይቁ እንደነበር የታወቀ ሲሆን የህገ ወጡ መጅሊስ አባላቶች ቆይ ትንሽ ጠብቁ አውሮፕላን ይመጣል በሚል ሃጃጆቹን ሲያንገሏቷቸው እንደነበር ተዘግቧል፡፡

ሃጃጆቹ ካረፉበት መካ ከተማ ወደ ጅዳ ኤርፖርት በመወሰዳቸው ማረፊያ ያጡ ሲሆን በጅዳ ኤርፖርት መሬት ላይ ካርቶን እያነጠፉ እንዲተኙ እንዳደረጓቸው ለፍትህ ራዲዬ ገልጸዋል

የሳኡዲ መንግስት በሂጃጆቹ ላይ እየደረሰ ያለውን እንግልት በመመልከት ለከፊል ሁጃጆቹ የሚያርፉበት ሆቴል የሰጣቸው ሲሆን የሁጃጁ ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ የተቀሩትን ለማስተናገድ አለመቻሉ ታውቋል፡፡

የኢትዬጲያ ሁጃጆች በርካታ አዛውንት አቅመ ደካሞች፣ሴቶች እና እናቶች ያሉበት ሲሆን ጅዳ ኤርፖርት ውስጥ መሬቱ ላይ ካርቶን ተነጥፎላቸው እንዲተኙ መደረጋቸው ተዘግበዋል፡፡

ይህ የተፈጸመባቸውን ግፍ በቪዲዬ የቀረፁ ሃጃጆች የነበሩ ሲሆን ከሁጃጆቹ መሃል ሁጃጅ መስለው የተቀላቀሉ ደህንነቶች እና ካድሬዎች ከህገ ወጡ መጅሊስ አመራሮች ጋር በመሆን ሁላችሁም የቀረፃችሁትን ቨዲዬ ባፋጣኝ አጥፉ፣ ይህን የማታደረጉ ከሆነ ወደ ሃገር አናሳፍራችሁም፣ ሃገር ከገባችሁም ቡኋላ ችግር ይገጥማቹሃል በማለት መሬት ላይ በካርቶን አንጥፈው የተኙትን ሃጃጆች በስልካቸው ላይ ያለውን ቪዲዬ እንዳስጠፏቸው ታውቋል፡

በጅዳ ኤርፖርት በተፈጠረው ውዝግብም የኢትዬጲያ አየር መንገድ አስተባባሪ ይህ ችግር ከአቅሜ በላይ ነው የሚል ምላሽ መስጠቱ የታወቀ ሲሆን በተፈጠረው አለመግባባትም የተወሰኑ ሃጃጆች ወደ ሃገራቸው በሌላ ሃገር አየር መንገድ እንዲሳፈሩ መደረጉን የፍትህ ራዲዬ ባልደረቦች ዘግበዋል፡፡

በሌላ ሃገር አየር መንገድ እንዲሳፈሩ የተደረጉት ሁጃጆችም ከለሊቱ 9 ሰአት ኢትዬጲያ ቢደርሱም እቃችሁ አልመጣም በሚል እስከ ቀኑ 4 ሰአት ድረስ ሲፈተሹ እና ሲዋከቡ እንደነበር ታውቋል፡፡

ሁጃጆቹ በስልካችሁ ላይ የቀረፃችሁት ቪዲዬ ካለ አጥፉ፣በስልካችሁ የደበቃችሁት ቪዲዬ ካለ ከባድ ችግር ይገጥማቹሃል በሚል ቦሌ አየር ማረፊያ ደህንነቶች ያስፈራሯቸው ሲሆን ስልካቸውን በመበርበር እና በመፈተሸ እስከ ቀኑ 4 ሰአት እንዳንገላቷቸው ታውቋል፡

በጅዳ የተከሰተውን ጉዳይ አስመልክቶ ለማንም ሚዲያ ምንም መረጃ እንዳትሰጡ በሚል ያስፈሯሯቸው ሲሆን ስልካቸውን እና ሌላ አድራሻቸውን እንደተቀበሏቸው ተዘግቧል፡፡

አሁንም ሁጃጆች እንግልት ላይ ሲሆኑ ከአህባሽ መራሹ መጅሊስ ጋር ቀረቤታ እና ትውውቅ ያላቸው ሁጃጆች ብቻ ቶሎ ወደ ሃገር እንዲመለሱ እየተደረጉ መሆኑ ታውቋል፡፡ በጅዳ ኤርፖርት በርካታ ቁጥር ያላቸው ኢትዬጲያውያን ሃጃጆች መሬት ላይ በካርቶን የተኙበትን ሁኔታ የሚያሳይ ቪዲዬ ለፍትህ ራዲዬ የደረሰ ሲሆን የዚህ መሰሉን ቪዲዬ ሁጃጆች ከስልካቸው ላይ በግዳጅ እና በማስፈራሪያ እንዲያጠፉ መደረጋቸው ታውቋል፡፡

አህባሽ መራሹ መጅሊስ የሃጅ ስነ ስርአት ከመጀመሩ በፊት ከኢትዬጲያ አየር መንገድ ጋር ውይይት አካሄድን፣የተለየ አግልግሎት ሊሰጡን ተስማማን እያለ በፌስቡክ ጭምር ፕሮፖጋንዳ ሲሰራ መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን ለህገ ወጡ መጅሊስ ሁጃጆች 70ሺህ ብር ከፍለው ቢሄዱም በርካታ ቁጥር ያላቸው ሃጃጆች በቆረጡት ቲኬት ቀነ ቀጠሮ መሰረት ወደሃገራቸው በሰላም ለመግባት እንዳልቻሉ ታውቋል፡፡

የሳኡዲ አረቢያ መንግስት ላለፉት 5 አመታት የሃጅ ክፍያ ምንም አይነት ጭማሪ አለማድረጉን ማስታወቁ የሚታወስ ሲሆን ህገ ወጡ መጅሊስ ግን የሳኡዲ መንግስት ክፍያ ጨምሮብን ነው በሚል ከባለፈው አመት 10ሺህ ብር ጭማሪ በማድረግ 70ሺህ ብር ከእያንዳንዱ ሃጃጅ በመቀበል በሚሊዬን የሚቆጠር ገንዘብ ከሃጃጆች መዝረፉ ታውቋል፡፡

ኢትዬጲያውያን ሃጃጆች አሁንም በጅዳ እንግልት ላይ መሆናቸው የታወቀ ሲሆን ወደሃገራችን በሰላም እንድንገባ ድምፃችንን አሰሙልን ሲሉ ሲሉ ጥሪያቸውን በፍትህ ራዲዬ በኩል አቅርበዋል፡፡

ከዚህ በታች የሚታየው ቪዲዬ ኢትዬጲያውያን ሁጃጆች በጅዳ ኤርፖርት መሬት ላይ በካርቶን እንዲተኙ የተደረገበትን ሁኔታ የሚያሳይ ነው

https://www.facebook.com/FITHRADIO/videos/788319351307488/