የኢብኑ ከሲር የቁርአን ሂፍዝ ማዕከል አመራሮች ቁርአን ሃፊዞችን ለማስመረቅ በሄዱበት መታሰራቸው ተዘገበ
ፍትህ ራዲዬ/ ግንቦት 16/2009
۩○◙◙○◙◙○◙◙○◙◙○۩
በአዲስ አበባ በሼህ ሆጀሌ መስጂድ ውስጥ የሚገኘው ግዙፉ የቁርአን ሂፍዝ ማዕከል የሆነው የኢብኑ ከሲር የቁርአን ሂፍዝ ማዕከል አመራሮች የቁርአን ሃፊዞችን ለማስመረቅ ወደ አሶሳ በተጓዙበት ለእስር መዳረጋቸውን የፍትህ ራዲዬ ባልደረቦች ዘግበዋል፡፡
የኢብኑ ከሲር የቁርአን ሂፍዝ ማዕከል የአሶሳ ቅርንጫፍ ቁርአን ሲያሳፍዛቸው የነበሩ ተማሪዎቹን ለማስመረቅ በአሶሳ ከተማ በሚገኘው የሰልፊያ መስጂድ ባዘጋጀው የምረቃ ስነ ስርአት ላይ ለመካፈል ከአዲስ አበባ ወደ አሶሳ ያቀኑት የመርከዙ ሃላፊዎች ለእስር መዳረጋቸው ታውቋል፡፡
በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ዋና ከተማ በሆነችው በአሶሳ ከተማ ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው የቁርአን ሃፊዞች የምረቃ ፕሮግራም በህገ ወጡ መጅሊስ እና በፖሊስ ሃይሎች እንዳይካሄድ መደረጉ ተዘግቧል፡፡
ይህን ተከትሎም በፕሮግራሙ ላይ ለመሳተፍ ከአዲስ አበባ የተጓዙት ኡስታዞች መንገድ ላይ ለእስር የተዳረጉ ሲሆን እስካሁን ታስረው እንደሚገኙ ተዘግቧል፡፡
የኢብኑ ከሲር የቁርአን ሂፍዝ ማዕከልን በሼህ ሆጀሌ መስጂድ የመሰረተው እና መርከዙን በበላይነት የሚመራው ኡስታዝ መሐመድ አብዱልቃድር(ባኮ)፣ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ(የመርከዙ ምክትል ሃላፊ) እና ሌሎች ወንድም እና ኡስታዞችም ለእስር መዳረጋቸው ታውቋል፡፡
በአሶሳ ከተማ በሰለፊያ መስጂድ ሊካሄድ የነበረው የሃፊዞች ምረቃ በመንግስት ታጣቂ ሃይሎች እንዳይካሄድ የተከለከለ ሲሆን በምረቃ ስነ ስርአቱ ላይ የተገኘውን ህዝበ ሙስሊም የፌደራል ልዩ ሃይሎች እንዲበተን ማድረጋቸው ታውቋል፡፡
የኢብኑ ከሲር የቁርአን ሂፍዝ ማዕከል የአሶሳ ቅርንጫፍ በሆነው መርከዝ ለ2አመት የቁርአን ሂፍዝ ሲማሩ የነበሩ ሲሆን እነዚህን ተማሪዎች ለማስመረቅ በሰለፊያ መስጂድ የተዘጋጀው ፕሮግራም በሃይል እንዲቆም መደረጉ ተዘግቧል፡፡
ኡስታዞቹ የታሰሩበት ምክንያት እስካሁን ግልፅ ያልሆነ ሲሆን ቁርአን የሃፈዙ ተማሪዎችን ለማስመረቅ በመጓዛቸው ለእስር መዳረጋቸው የእምነት ነፃነት ጉዳይ በኢትዬጲያ እየተዳፈነ መምጣቱን አመላካች መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
በተመሰሳይ ዜናም የህዝበ ሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ የህግ ጉዳዬች ተጠሪ የሆኑት ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ ለ2 ቀናት በማዕከላወ ታስረው መፈታታቸውን የፍትህ ራዲዬ ባልደረቦች ዘግበዋል፡፡
ኡስታዝ ካሚል ሸምሱን ጨምሮ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ እና ኡስታዝ ያሲን ኑሩ ባሳለፍነው ጁምዓ ግንቦት 11/2009 ከጠዋቱ 3.30 ላይ በማዕከላዊ እንደሚፈለጉ ተገልፆላቸው ወደ ማዕከላዊ ማምራታቸው ታውቋል፡፡
በማዕከላዊም ኡስታዝ አቡበከር አህመድ፣ኡስታዝ ያሲን ኑሩ እና ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ ተጠርተው እያደረጉት ያለውን የዳዕዋ እንቅስቃሴ ማቆም እንደሚኖርባቸው የተነገራቸው ሲሆን ኡስታዝ አቡበከር አህመድ እና ኡስታዝ ያሲን ኑሩ በእለቱ ሲለቀቁ ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ ግን ለሁለት ቀናት በማዕከላዊ ታስረው እንዲቆዩ መደረጋቸው ተዘግቧል፡፡
ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ የቤተል ተቅዋ መስጂድ ኢማም መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን በየሳምንቱ ጁምዓ የህዝበ ሙስሊሙን ልብ የሚኮረኩሩ ወቅታዊ ትምህርቶችን በኹጥባቸው በማቅረብ ይታወቃሉ፡፡
ኡስታዝ ካሚል ለሁለት ቀናት በማዕከላዊ ታስረው እንዲቆዩ ከተደረገ ቡሃላ ግንቦት 13 እለተ እሁድ እንዲፈቱ የተደረገ ሲሆን ሁሉም ኡስታዞች በየቦታው ሙስሊሙ ለዲኑ እና ለሃገሩ መልካም መዋል እንደሚኖርበት እያስተማሩ ቢገኙም ይህን የዳዕዋ ተግባራቸውን እንዲያቆሙ በማዕከላዊ መርማሪዎች እና ደህንነቶች እንደተነገራቸው ተዘግቧል፡፡
ህገ ወጡ መጅሊስ የመስጂድ ምረቃ፣የቁርአን ሃፊዞች ምረቃ እና የተለያዩ ዲናዊ ፕሮግራሞች እንዲቆሙ ለመንግስት እርዳታ መጠየቁ የሚታወቅ ሲሆን እየተካሄዱ ያሉት ፕሮግራሞች የአክራሪዎች ነው የሚል መንግስት እርምጃ እንዲወስድ አህባሽ መራሹ መጅሊስ በተደጋጋሚ መጠየቁ ይታወቃል፡፡

ተጨማሪ ምስል