የኡስታዝ አህመዲን ጀበል "ሶስቱ አፄዎች" የተሰኘው መፅሃፍ የተገኘበት ሙስሊም ታሳሪ " የህዝብን አመለካከት ለማናወጥ" በሚል ክስ እንደተመሰረተበት ተዘገበ
ፍትህ ራዲዬ/ ጥር 4/2009
۩○◙◙○◙◙○◙◙○◙◙○۩
ባሳለፍነው አመት በነሀሴ 6 ቀን 2008 በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ ዞን በሚገኙ ከተማዎች በተካሄደው አፈሳ ለእስር ተዳርገገው ከነበሩ በርካታ ሙስሊም እስረኞች መካከል የኡስታዝ አህመዲን ጀበል "ሶስቱ አፄዎች" የተሰኘው መፅሃፍ የተገኘበት ሙስሊም ታሳሪ" የህዝብን አመለካከት ለማናወጥ" የሚል ክስ ተመስርቶበት እንደነበር የፍትህ ራዲዬ ባልደረቦች ዘግበዋል፡፡
በደቡብ ወሎ ዞን አሁንም ድረስ በርካታ ሙስሊሞች እየታፈሱ መሆናቸውን መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን ወደ ኮምቦልቻ ማረሚያ ቤት እና ወደ ጦላይ የጦር ማሰልጠኛ እየተወሰዱ መሆናቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
በ 2008 በ በመላው የወሎ ከተማዎች በተካሄደው አፈሳ ከደሴ ሰኞ ገበያ አካባቢ ከመኖሪያ ቤቱ የታፈነው ወጣት ሁሴን አራጌ የሚገኝበት ሲሆን ወጣት ሁሴን አራጌ በተያዘበት ወቅት ፓሊስ በማስረጃነት ፣ የአህመዲን ጀበል "ሶስቱ አፄዎች" ፣ የፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ "የኦሮሞና አማራ የዘር ግንድ" ፣ እንዲሁም ሌሎች የታሪክ መፅሀፍቶች እና የግል ማስታወሻ ወረቀቶች እንደተያዘበት ለማወቅ ተችሏል፡፡
ፖሊስ በፍተሸ ወቅት በቤቱ ያገኛቸውን የታሪክ መፅሃፍቶች በመውሰድ ሃሰተኛ ክስ ለማዘጋጀት ሲጥር የቆየ ሲሆን ከወጣት ሁሴን አራጌ ጋር 22 የሚደርሱ እስረኞችን ለ 81 ቀናት በደሴ ከተማ ማረሚያ ቤት እንዲታሰሩ ማድረጉ ተዘግቧል፡፡
ፖሊስ በግፍ ለ 81 ቀናት እንዲታሰሩ ካደረገ ቡሃላ በዋስ እንዲፈቱ ያደረገ ሲሆን አቃቤ ህጉም በደሴ ወረዳ ፍ/ቤት የወንጀል ህጉን አንቀፅ 486/ (ሀ እና ለ) በመጥቀስ " የህዝብን አመለካከት ለማናወጥ" የሚል ክስ እንደመሰረተባቸው ተዘግቧል፡
ወጣት ሁሴን አራጌ የቀረበበትን ሃሰተኛ ክስ በመቃወም በደሴ ወረዳ ፍርድ ቤት ሲከራከር የቆየ ሲሆን ፍርድ ቤቱ ህዳር 16 በዋለው ችሎት አቃቢ ህግ ያቀረባቸውን መፀሀፍትና በቁርጥራጭ ወረቀት የተፃፉ ማስታወሻዎች በመመርመር ተከሳሽ ሁሴን አራጌን ለሁለት አመት ማንኛውንም ፅሁፍ ከመፃፍ እንዲታደግ የወሰነበት ሲሆን ከአሁን በፊት የታሠረውንና የቤተሰብ አስተዳዳሪነቱን ከግምት በማስገባት የአምስት መቶ ብር የገንዘብ መቀጮም እንደጣለበት ተዘግቧል፡፡
የኡስታዝ አህመዲን ጀበልን እና መሰል የታሪክ መፅሃፍን በመያዙ " የህዝብን አመለካከት ለማናወጥ" ሞክረሃል በሚል ህገ መንግስታዊ መብቱ የተገፈፈ ሲሆን ለሁለት አመት በተጣለበት እገዳ እና በደህንነቶች በሚደረግበት ጫና ቤተሰቡን ጥሎ መሰደዱን የቤተሰቡ ምንጮች ለፍትህ ራዲዬ ገልጸዋል፡፡
በደቡብ ወሎ ባሉ ከተሞች በርካታ ወጣቶች እየታሰሩ እና እየተንገላቱ የሚገኙ ሲሆን ስደትን ብቸኛ አማራጭ በማድረግ እየተሰደዱ መሆናቸው ታውቋል፡፡

ተጨማሪ ምስል