የአንጋፋው የወልዲያው ሰላም መድረሳ የ 3አመት ሙሉ ባጀቱን ሼህ መሐመድ ሁሴን አልአሙዲን እንደሚሸፍኑ ቃል ገቡ
ፍትህ ራዲዬ/ ጥር 7/2009
۩○◙◙○◙◙○◙◙○◙◙○۩
በአማራ ክልል በሰሜን ወሎ ዞን በወልዲያ ከተማ ከአወልያ ቀጥሎ ግዙፉ የሙስሊሙ ተቋም የነበረው የወልዲያ መስጂዶች እና ትምህርት ቤቶች ማዕከል በህገ ወጡ መጅሊስ እና በመንግስት ለአህባሾች እንዲሰጥ ከተደረገ በኋላ ተቋሙን የማዳከም ስራ ሲሰራ መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን በማዕከሉ ስር የነበረውን የሰላም መድረሳን የአካዳሚኩን ክፍል ህዝባዊ ኮሚቴው እንዲያስተዳድረው በማድረግ ከፍተኛ የበጀት እጥረት እንዲከሰትበት በህገ ወጡመጅሊሶች ሲደረግ መቆቱ ይታወሳል፡፡
ማዕከሉ በስሩ የነበሩ የገቢ ማስገኛዎቹን በሙሉ አህባሽ መራሹ መጅሊስ በመውረሱ ትምህርት ቤቱ በአቅም ማነስ ምክንያት ለመዘጋት አደጋ ላይ ወድቆ የነበረ ሲሆን የማዕከሉ መስራች የሆኑት ሃጂ ሲራጅን ጨምሮ ሌሎች በመረባረብ በሳኡዲ አረቢያ ለ 2 ጊዜ ያህል ለመድረሳው ድጋፍ የሚሆን የገቢ ማሰባሰቢያ እንዲካሄድ ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡
ሰላም ትምህርት ቤት ከፍተኛ ወጪ ያለበት በመሆኑ አመታዊ በጀቱ ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቅ የነበረ ሲሆን የወልዲያ ስታዲዬምን ያስገነቡት ባለሃብት ሼህ መሐመድ ሁሴን አል አሙዲን መድረሳውን ከጎበኙ ቡሃላ የ3አመት ወጪውን ለመሸፈን ቃል መግባታቸውን የፍትህ ራዲዬ ባልደረቦች ዘግበዋል፡፡
ሼህ መሐመድ ሁሴን አል አሙዲን የወልዲያ ተወላጅ ሲሆኑ ከሰላም ት/ቤት መስራች ከሆኑት ከሃጂ ሲራጅ ጋር አብሮ አደግ መሆናቸውን መድረሳውን በጎበኙበት ወቅት ገልፀዋል፡፡
መድረሳው አሁን ያለበትን ችግር አሁን ተረድቻለው ያሉት ሼህ መሀመድ በቀጣይም መድረሳው በቋሚነት የራሱ የሆነ የገቢ ማስገኛ ስለሚያስፈልገው ለሱ የሚሆን ተቋም ማኖር ይኖርብናል ማለታቸው ተዘግቧል፡፡
በማዕከሉ ስር የነበረው የሰላም ሆቴል ኢስላማዊ ትምህርት ቤትን ለመደጎም መዋሉ አግባብ አይደለም ያሉ ሲሆን በሆቴሉ ብዙ ሃራም ስራ በሚሰራበት ገንዘብ ኢስላማዊ ትምህርት ቤቱን መደጎም ደስ የሚል ባለመሆኑ ከሆቴል ሌላ ለመድረሳው ገቢ የሚሆን ተቋም እንደሚመሰረት መግለፃቸው ተዘግቧል፡፡
ከ 1965 ጀምሮ የወልዲያን ሙስሊም ማህበረሰብ ሲያገለግል የቆየው ይህ ተቋም በርካታ ምሁራንን እና ለሃገር የሚጠቅሙ ዜጎች ያፈራ ሲሆን የዲን እውቀትም ተማሪዎች ከልጅነታቸው ጀምሮ በማስተማር በአካዳሚክም በመንፈሳዊ እውቀትም የበለፀጉ እንዲሆኑ ሲያደርግ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
የአህባሽ መራሹ መጅሊሽ በሰላም መድረሳ የሚሰጠውን ትምህርት የአካዳሚክ እና የዲን ትምህርቱ እንዲለይ ከመንግስት ጋር በመተባበር ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን የአካዳሚክ ትምህርቱን በህዝባዊ ኮሚቴው እንዲመራ በማድረግ የዲን ትምህርቱን ደግሞ በአህባሽ መራሹ መጅሊስ እንዲመራ ማድረጋቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ተጨማሪ ምስል