የቂሊንጦ ማ/ቤት እንዲቃጠል ምክንያት ሆነዋል በሚል 38 እስረኞች ክሰ እንደተመሰረተበቸው ታወቀ

ፍትህ ራዲዬ/ኅዳር14/2009
۩○◙◙○◙◙○◙◙○◙◙○۩

የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በእሳት አደጋ ጉዳት ከደረሰበት ቡኋላ ማረሚያ ቤቱን ያቃጠልነው እና ነን ብላችሁ እመኑ በሚል በሸዋሮቢት ማረሚያ ቤት ከፍተኛ ድብደባ እና ስቃይ ሲያስተናግዱ የነበሩት እስረኞች ክስ እንደተመሰረተባቸው የመንግስት ሚዲያ የሆነው ፋና ብሮድካስቲንግ አስታውቋል፡፡

ፋና በዘገባው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት በተከፈተው ክስ፥ ታራሚዎቹ 10 ሚሊየን ብር የሚገመት ንብረት እንዲወድም አድረገዋል ሲል ክስ እንደተመሰረተባቸው ገልፆል፡፡

በዚህ ክስ የተወነጀሉትበሸብር ወንጀል ክስ የተመሰረተባቸው ተከሳሾች 1ኛ ማስረሻ ሰጤ፣ 2ኛ ወልዴ ሞቱማ፣ 3ኛ አሸናፊ አካሉ ጨምሮ 38 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የሚገኙ  መሆናቸውን ዘግቧል፡፡

ተከሳሾቹ ከጥር ወር 2008 ዓ. ጀምሮ የኦነግ፣ ግንቦት ሰባት እና በአልሸባብ የሽብር ቡድን ተልዕኮ ለመፈጸም በማረሚያ ቤቱ በተለያዩ ወንጀሎች በእርማት ላይ ያሉ ታራሚዎችን በድብቅ በመመልመል አመጽ ለመፍጠር መረጃ መለዋወጣቸውን የጠቅላይ አቃቢ ህግ ክስ እንደሚያስረዳ ተገልፆል፡፡

አመጽ ማስነሳት እንዲችሉም በውጭ እና ሃገር ውስጥ ከሚገኙ አባላትና ማረሚያ ቤት ውስጥ ከሚገኙ ታራሚዎች ገንዘብ በማሰባሰብ የአመጹን ድርጊት በሃይል ይመራሉ ብለው ለመለመሏቸው ታራሚዎች ከተሰበሰበው ገንዘብ በተለያየ ጊዜ ክፍያ እንዲፈጸም ማድረጋቸውም በክሱ ተጠቅሷል።

በተለያየ ጊዜ በድብቅ መረጃ በመለዋወጥ የአመጽ ጥሪ በማስተላለፍ በማረሚያ ቤቱ አመጽ ማስነሳት፣ ማቃጠልና ማውደም የሚል እቅድ በመያዝ በነሃሴ 28 ቀን 2008  ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ላይ የዞን ሁለት ታራሚዎች ባስነሱት አመጽ የዋጋ ግምቱ 10 ሚሊየን ብር የሚገመት የማረሚያ ቤቱን ንብረት አውድመዋል ሲል ክስ መመስረቱ ታውቋል፡፡

በቂሊንጦ ማረሚ ቤት የእሳት ቃጠሎ ከተከሰተ ቡኋላ ከእስር ቤቱ ለማምለጥ ሞክረዋል በሚል ቁጥራቸው ከ 23 በላይ እስረኞች በግፍ በጥይት ተመተው መገደላቸው የሚታወቅ ሲሆን  ይህንንም የሞቱትን እስረኞች ደብድበው በእሳት ያቃጠሉት እነዚህ 38 እስረኞች ናቸው በሚል ክሱ ላይ እንደሰፈረ ተገልፆል፡፡

የክስ መዝገቡ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት የቀረበ ሲሆን፥ ማረሚያ ቤቱ ተከሳሾቹን ችሎት ሲያቀርብ ፍርድ ቤቱ የክስ ቻርጁን የሚያሰማ መሆኑ ተዘግቧል፡፡

ከተከሰሱት እስረኞች መካከል በሼህ ኑሩ ግድያ፣በከድር መሐመድ የክስ መዝገብ እና በነብዩ ሲራጅ መዝገብ የተከሰሱ ሙስሊሞች እንደሚገኙበት ታውቋል፡፡

በሸዋሮቢት ማረሚያ ቤት በማዕከላዊ መርማሪ ፖሊሶች ከፍተኛ ስቃይ እና ድብደባ እየተፈፀመባቸው ማረሚያ ቤቱን ያቃጠልነው እኛ ነን ብላችሁ እመኑ በሚል በግዳጅ ማስፈረማቸው ይታወቃል፡፡

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይም እስረኞቹን ከሸዋሮቢት ወደ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት እንዲዘዋወሩ ያደረጓቸው ሲሆን

ከሸዋሮቢት ወደ ቂሊንጦ ከተመለሱት መካከል  ኡስማን አብዶ፣ ሸህአብዲን ነስረዲን፣ ፍፁም ቸርነት፣ ኢብራሂም ካሚል፣ ከድር ታደለ፣ ኡመር ሁሴን ፣  እስማኤል ሀሰን እና ነዚፍ ተማም እንደሚገኙበት ታውቋል፡፤

ከሸዋሮቢት ወደ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት እንዲዘዋወሩ ቢደረጉም ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዳይገናኙ መከልከላቸውን  የፍትህ ራዲዬ ባልደረቦች ዘግበዋል፡፡

በሸዋሮቢት ማረሚያ ቤት ከማዕከላዊ የመጡ መርማሪዎች  ከፍተኛ ድብደባ በመፈጸም እና ፂማቸውን በመላጨት ሰብአዊ ክብራቸውን በጣሰ መልኩ ሲያሰቃዩዋቸው እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን  የቂሊንጦ ማረሚያ ቤቱን ያቃጠልነው እኛ ነን ብለው በግዳጅ እንዲናገሩ ሲደረጉ እንደነበር ይታወቃል፡፡