የቂሊንጦ ማ/ቤትን አቃጥላቹሃል በሚል ክስ የተመሰረተባቸው 38 እስረኞች ለታህሳስ 14 ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጣቸው

ፍትህ ራዲዬ/ኅዳር23/2009

۩○◙◙○◙◙○◙◙○◙◙○۩

በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ቃጠሎ እንዲነሳ አድረገዋል በሚል እና 23 ታራሚዎች ላይ አሰቃቂ ድብደባ ፈፅመው በእሳት እንዲቃጠል አድርገዋል በሚል የሃሰት ክስ የተመሰረተባቸው 38 እስረኞች በዛሬው እለት አርብ ህዳር 23 የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ መቅረባቸውን የፍትህ ራዲዬ ባልደረቦች ዘግበዋል፡

በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ የወንጀል ችሎት ክስ የተመሰረተባቸው 38ቱ እስረኞች አቃቤ ህጉ የመሰረተባቸውን የሃሰት ክስ በዛሬው ችሎት በንባብ የቀረበላቸው ሲሆን በተለያየ ጊዜ በድብቅ መረጃ በመለዋወጥ የአመጽ ጥሪ በማስተላለፍ በማረሚያ ቤቱ አመጽ ማስነሳት፣ ማቃጠልና ማውደም የሚል እቅድ በመያዝ በነሃሴ 28 ቀን 2008 ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ላይ የዞን ሁለት ታራሚዎች ባስነሱት አመጽ የዋጋ ግምቱ 10 ሚሊየን ብር የሚገመት የማረሚያ ቤቱን ንብረት አውድመዋል ሲል አቃቤ ህጉ ክስ ማቅረቡ ታውቋል፡፡

በውጭና በአገር ውስጥ ከሚገኙ ታራሚዎች ገንዘብ በማሰባሰብ የአመፁን ድርጊት በኃይል ይመራሉ ያሉዋቸውን በከባድ ወንጀልና በውንብድና የተከሰሱትን ታራሚዎች በመመልመል፣ ‹‹የሽብርና የዱርዬው ቡድን›› የሚል ስያሜ በመስጠት ሲመካከሩ ከርመዋል ሲል አቃቤ ህጉ በክሱ ላይ ማቅረቡ ተዘግቧል፡፡

በተጨማሪም በመንግስት ወታደሮች የተገደሉትን 23 እስረኞች በተከሳሾቹ ላይ በማላከክ አሰቃቂ በሆነ መልኩ በመደበደብ በእሳት እንዲቃጠሉ አድረገዋል በሚልም አቃቢ ህጉ ክስ መስርቶባቸዋል፡፡

አቃቤ ህጉ ክስ ከመሰረተባቸው መካከል በሙስሊሙ ሰላማዊ ትግል የታሰሩት ኢብራሂም ካሚል፣ፍፁም ቸርነት፣ሸህቡዲን ነስረዲን፣ከድር ታደል አና ኡመር ሁሴን እንደሚገኙበት ይታወቃል፡፡

ተከሳሾቹ የክስ ቻርጁ ከተነበበላቸው በኋላ በግል ወይም በመንግስት ጠበቃ መወከል እንዳለባቸው ተማክረው እንዲቀርቡ ፍርድ ቤቱ ለታህሳስ 14 ቀን 2009 ተለዋጭ ቀጠሮ በመስጠት ችሎቱ መጠናቀቁን የፍትህ ራዲዬ ባልደረቦች ዘግበዋል፡፡

ተጨማሪ ምስል