የቂሊንጦ ማ/ቤትን በሃሰት አቃጥላቹሃል በሚል በተወነጀሉት እስረኞች ላይ በሐሰት እንዲመሰክሩ የተስማሙ ፖሊሶች በዋስ መለቀቃቸው ተዘገበ
ፍትህ ራዲዬ/ ግንቦት 6/2009
۩○◙◙○◙◙○◙◙○◙◙○۩
 
የቂሊንጦ ማረሚያ ቤትን አቃጥለዋል በሚል በሐሰት በተወነጀሉ እስረኞች ላይ አቃቤ ህጉ በሃሰት እንዲመሰክሩለት ካቀዳቸው ምስክሮች መካከል ለእስር ላይ የነበሩ የፖሊስ አባላት እንደሚገኙበት የተዘገበ ሲሆን በሐሰት እንዲመሰክሩ በመስማማታቸው ከእስር መለቀቃቸውን የፍትህ ራዲዬ ባልደረቦች ዘግበዋል፡፡
በማረሚያ ቤቱ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎም ወደ ማረሚ ቤቱ በሚሊዬን የሚቆጠር ገንዘብ በድብቅ አስገብተዋል በሚል የተወሰኑ ፖሊሶች ለእስር ተዳርገው የቆዩ ሲሆን በማዕከላዊ መርማሪዎች በተሰጣቸው ትዕዛዝ መሰረት በተከሳሾቹ ላይ በሐሰት ለመመስከር መስማማታቸው ተዘግቧል፡፡
ፋሲል የተባለን የፖሊስ አባል ጨምሮ ሌሎች አብረውት የታሰሩት ፖሊሶች በሃሰት በተወነጀሉት እስረኞች ላይ ለመመስከር መስማማታቸው የታወቀ ሲሆን በተስማሙት መሰረትም በዋስ ከእስር እንዲለቀቁ መደረጉ ተዘግቧል፡፡
ከፖሊስ ምስክር በተጨማሪ ሌሎች እስረኞች በሀሰት እንዲመሰክሩ እየተገደዱ መሆናቸው የተዘገበ ሲሆን በሐሰት እንዲመሰክሩ ከተመለመሉት መካከል የመንግስት አቃቤ ህጉ በሚፈልገው መልኩ አንመሰክርም ያሉ ከፍተኛ ድብደባ እየተፈፀመባቸው እንደሚገኝ ታውቋል፡፡
እየተፈፀመባቸው ያለው ድብደባ ከአቅማቸው በላይ መሆኑን የገለፁ ሲሆን በንፁሃን እስረኞች ላይ አስገድደው በሃሰት ሊያስመሰክሯቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ከነዚህ ምስክሮች በተጨማሪም በሌላ ክስ ተከሰው ወደ ማረሚያ ቤቱ የገቡ እስረኞችን ወደ ቃሊቲ ዞን8 እንዲዘዋወሩ በማድረግ በሃሰት እንዲመሰክሩ አቃቤ ህጉ ያግባባቸው ሲሆን በሀሰት ከመሰከሩ የቀረበባቸው ክስ ተቋርጦ ከእስር እንደሚፈቱ ቃል እንደተገባላቸው ተሰምቷል፡፡
አቃቤ ህጉ በቂሊንጦ ቃጠሎ ባቀረበው ክስ ላይ ተከሳሾቹ ወንጀሉን መፈፀማቸውን አምነዋል በሚል የሰጡትን ቃል እንደማስረጃ ማቅረቡ የሚታወስ ሲሆን በቃጠሎ ወንጀል የተወነጀሉት አስረኞች ግን ተገደው እና ከአቅማቸው በላይ ሆኖ ቃላቸውን መስጠታቸውን ለፍርድ ቤቱ ማስረዳታቸው ይታወሳል፡፡
በሸዋሮቢት እና በዝዋይ ማረሚያ ቤቶች እጅግ አሰቃቂ ድብደባ እና ስቃይ እንደተፈጸመባቸው ለፍርድ ቤቱ በማስረዳት የቀረበባቸው መስረጃ ውድቅ እነዲሆን መጤቃቸው ይታወቃል፡፡
ተከሳሾቹ አንዱን ተሰቃይ አደራጅ ሌላውን ተደራጅ በማስመሰል አማራ፣ ጉራጌ እና ደቡቡን የግንቦት 7 አደራጅ፤ ኦሮሞውን የኦነግ አደራጅ፤ በሐይማኖት ነፃነት ጥያቄ የገቡ ሙስሊሞችን የአልሸባብ አደራጆች፤ ድሃውን የአዲስ አበባ ወጣት ደግሞ ከላይ በተጠቀሱት ተደራጅ እና ሀገራቸውን በህክምና ሊያገለግሉ ከስዊድን አገር ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የአዲስ የልብ ህክምና ባለቤት የሆኑትን ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ እና በሙስና ተጠርጥሮ የታሰረው ሚስባህ ከድርን የገንዘብ ምንጭ (ደጋፊ) በማስመሰል በነሀሴ 28 ቀን 2008 በቃጠሎው ዕለት ዶ/ር ፍቅሩ ባዘጋጁት 60 መኪኖች በጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል አካባቢ እንዲቆም ተደርጎ ከእስር ቤት አምልጠን በአምስት አቅጣጫ (በጎንደር በአሶሳ በሞያሌ በኢትዮጵያ ሶማሌ) አድርጋችሁ ወደ ኤርትራ በመሄድ ከአሸባሪ ድርጅቶች ጋር ልትገናኙ አስባችኋል፣ ቂ/ማ/ቤት አቃጥላችኋል የሚል ሰነድ በማዘጋጀት የእኛ ያልሆነ ቃል እንድንፈርም ተደርጎ ፅሁፉንም እያጠናን እንድንለማመድ ከተደረገ በኋላ ቪዲዮ የተቀረፅን ሲሆን እርስ በርስ ከስቃይ ብዛት እንድንገናኝ እያደረጉ “አደራጅቻለሁ፣ ገንዘብ ሰጥቻለሁ፣ ኤርትራ ልንሄድ ነበር፣ ከእስር ቤት ልናመልጥ ነበር” እንድንባባል መደረጉን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡
ይህም ሆኖ በፍ/ቤት ህገ መንግስታዊ መብቶቻችን ተጥሰዋል ሲሉ ተከሳሸች አቤቱታቸውን ያቀረቡ ሲሆን ከዚህም መካከል 1ኛ በግዳጅ የተገኘ ቃል በህገ መንግስቱ የተከለከለ መሆኑን አስረድተን በ27/2 መሰረት በሲቃይ ብዛት የሰጠነው ቃል ውድቅ ይደረግልን፤2ኛ ያሰቃዩንን እና ኢሰብዓዊ ድርጊት የፈፀሙብንን የመርማሪ ፖሊሶች የማ/ቤት አመራር እና ፖሊሶች መክሰስ እንድንችል ፖሊስ ቃላችን እንዲቀበለን፤ 3ኛ አካላችን ላይ የነበረው ጠባሳ ፎቶ ግራፍ እንድንነሳ፤ 4ኛ የቂሊንጦ ቃጠሎ መንስኤውን ገለልተኛ ወገን እንዲያጣራው ፍ/ቤቱ እንዲያዝ እና ፍርደኞች ወደ ፍርድ ክልል (ቃሊቲ) እንዲሄዱ ተደርጎ ክሳችንን ከዚያ ሆነን እንድንከታተል ያቀረብነው አቤቱታ እና የህይወት ዋስትና እንዲሰጠን አቤቱታ ያቀረቡ ቢሆንም ፍ/ቤቱ አንድም ነገር ሳይበይን ለግንቦት 14 ዓቃቢ ህግ በሃሰት ያደራጃቸውን ምሰክሮች ለመስማት ቀነ ቀጠሮ መስጠቱን ገልፀዋል፡፡
ማ/ቤቱም ለምን አቤቱታ አቀረባችሁ በማለት 37 ሰዎችን 4 በ5 በሆነች ጠባብ ቤት ውስጥ ጨለማ ክፍል ከ2 ወር በላይ በመቆየት አሰቃይተውናል ሲሉ የገለፁ ሲሆን ፡ከዚሁ ቃጠሎ ጋር በተያያዘ በተጨማሪ 121 ሰዎች ልደታ 3ኛ ወንጀል ችሎት ሌላ ክስ እንደመሰረቱ ተከሳሾቹ ገልፀዋል፡፡
በዚህ ሁኔታ ላይ እያሉ ፍርድ ቤቱ በግንቦት 14 የአቃቤ ህጉን ምስክሮች ለማድመጥ ቀነ ቀጠሮ መስጠቱ ተዘግቧል፡፡

ተጨማሪ ምስል