ከ166በላይ ስደተኞች በሜዴትራንያን ባህር ሰምጠው መሞታቸው ተዘገበ
ፍትህ ራዲዬ/ ጥር 18/2009
۩○◙◙○◙◙○◙◙○◙◙○۩
ከሊቢያ ወደ ጣሊያን ከ170 በላይ የሚሆኑ ስደተኞችን ከአቅሙ በላይ የጫነ ጀልባ ቅዳሜ ለሊት በሚዲትራኒያን ባህር ሰምጦ አራት ስደተኞች ብቻ ሲተርፉ ሌሎቹ ህይወታቸውን ማጣታቸውን አንድ የስደተኞች መርጃ ድርጅት አስታወቀ።
ከተረፉት ስደተኞች ሁለቱ ኤርትራዊ ሁለቱ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ሲሆኑ አንዷ ነፍሠ ጡር እንደሆነች አጀንሲያ አበሻ የተባለው ስደተኞችን የሚረዳው ቡድን መሪ አባ ሙሴ ዘርዓይ፤ የጣሊያን ባህር ሃይልን ጠቅሰው ገልጸዋል፡፡
አዲሱ የፈረንጆች አመት ከገባ ወዲህ የዚህ መሰሉ አደጋ ለሁለተኛ ጊዜ የተከሰተ ሲሆን ባሳለፍነው ቅዳሜ በደረሰ አደጋ 160 የሚደርሱ ስደተኞች ባህር ውስጥ ገብተው መሞታቸው ተዘግቧል፡፡
ስደተኞቹ ከኢትዬጲያ፣ከኤርትራ፣ከሱዳን ፣ከሶማልያ እና ከሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ወደ አውሮፓ ለማቅናት ሲሞክሩ የነበሩ መሆናቸው የተገለፀ ሲሆን ጀልባው መያዝ ከሚችለው በላይ ስደተኞች በመጫናቸው ጀልባው ተገልብጦ በርካቶችህይወታቸው ማለፉ ተዘግቧል፡፡
ከሞቱት መካከል በርካታ ሴቶች እንደሚገኙበት የታወቀ ሲሆን አንድ ነፍሰ ጡረ የሆነች ሴት በህይወት መትረፏ ታውቋል፡፡
ከስደተኞቹ መካከል ቁጥራቸው 8 የሚደርሱ ህፃናትም እንደነበሩ የተገለፀ ሲሆን በአደጋው ህይወታቸውን ያጡት ስደተኞች ቁጥር ከ 166 ሊበልጥ እንደሚችል ተዘግቧል፡፡
በአሁኑ ወቅት የሜዴትራንያን ባህር ከፍተኛ የባህር ሞገድ ያለበት ሲሆን ህገ ወጥ ደላሎች የባህሩን የማዕበል ሁኔታ አደገኛ መሆኑን እያወቁም ስደተኞቹ በደካማ ጀልባ እንዲጓዙ በማድረግ ለህልፈተ ህይወት እንዲጋለጡ እንዳደረጓቸው ታውቋል፡፡
በኢትዬጲያ እና በአፍሪካ ሀገራት ባለው ጭቆና እና ድህነት በርካታ አፍሪካውያን ለስደት እየተዳረጉ ሲሆን በባህር ውስጥም ሰምጠው በርካቶች ህይወታቸው እያለፈ እንደሚገኝ ተዘግቧል፡፡

ተጨማሪ ምስል