አሳዛኝ ዜና-ፍትህ ራዲዬ
በአዲስ አበባ በቂርቆስ ክ/ከተማ በአዲሱ ወረዳ 8 የሚገኘው ተውባ መስጂድ ቦታው ለልማት ተፈልጓል በሚል ሊፈርስ መሆኑ ተገለፀ
ፍትህ ራዲዬ/ የካቲት 19/2009
۩○◙◙○◙◙○◙◙○◙◙○۩
በአዲስ አበባ በቂርቆስ ክ/ከተማ በአዲሱ ወረዳ 8 ውስጥ የሚገኘው ተውባ መስጂድ ቦታው ለልማት ተፈልጓል በሚል በመንግስት አካላት ሊፈርስ መሆኑን የፍትህ ራዲዬ ባልረቦች ዘግበዋል፡፡
የተውባ መስጂድ በካሳንችስ ቁጥር 2 መልሶ ማልማት ክልል ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ መስጂዱ እንደሚፈርስ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማት እና ከተማ ማደስ ኤጀንሲ ማስታወቁ ተገልፆል፡፡
መስጂዱ ላለፉት 30 አመታት የአካባቢውን ሙስሊም ማህበረሰብ ሲያገለግል የኖረ መስጂድ ሲሆን ቦታው ለልማት ተፈልጓል በሚል እንዲፈርስ እንደተወሰነበት ታውቋል፡፡
የተውባ መስጂድ ኮሚቴዎች ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማት እና ከተማ ማደስ ኤጀንሲ በ29/03/2009 ደብዳቤ በመፃፍ መስጂዱ ለ30 አመታት የአካባቢውን ሙስሊም ማህበረሰብ እያገለገለ የሚገኝ በመሆኑ የመስዱን ይዞታ ለማልማት ኮሚቴው እንዲፈቀድለት ጥያቄ ማቅረቡ ተዘግቧል፡፡
ሆኖም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማት እና ከተማ ማደስ ኤጀንሲ የመስጂዱ ኮሚቴዎች ያቀረቡትን የልማት ጥያቄ ውድቅ በማድረግ መስጂዱ እንደሚፈርስ እንዳስታወቃቸው የፍትህ ራዲዬ ባልደረቦች ዘግበዋል፡፤
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማት እና ከተማ ማደስ ኤጀንሲ በፃፈው በብዳቤ አካባቢው ባለ 5 ኮከብ ሆቴል እና ከሱ ጋር ተያይዞ ለሚመጣ ሞልሾፒንግ የተዘጋጀ በመሆኑ፣ በመሪ ፕላኑ ላይ መስጂድ በአካባቢው እንዲቀጥል ያልተደረገ በመሆኑ መስጂዱ በቦታው እንዲቀጥል የማይፈቀድ መሆኑን እና ሙስሊሙ የመስጂዱን ይዞታነት ለማልማት ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት የሌላው መሆኑን አስታውቋል፡፡
በአዲስ አበባ ከቦሌ ጀምሮ በከተማው ግንባር ቦታዎች ላይ የነበሩ መስጂዶች በልማት ስም እንዲፈርሱ እየተደረገ መሆኑ የተዘገበ ሲሆን በመሪ ፕላኖች ላይ መስጂዶች እንዲኖሩ ታቅዶ ባለመዘጋጀቱ የከተማው ህዝበ ሙስሊም ሲገለገልባቸው የነበሩ መስጂዶች በግዳጅ እንዲፈርሱ እየተደረገ መሆኑ ተዘግቧል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማት እና ከተማ ማደስ ኤጀንሲ ለተውባ መስጂድ ኮሚቴዎች ጥያቄያቸውን ውድቅ ማድረጉን የገለጸበት ደብዳቤ ከዚህ በታች ተያይዞ ቀርቧል

ሃስቡን አላህ ወኒ አመል ወኪል

ተጨማሪ ምስል