በደቡብ ወሎ በማሻ መቅደላ በርካታ ሙስሊሞች ዳግም እየታሰሩ መሆኑ ተዘገበ
ፍትህ ራዲዬ/ የካቲት 22/2009
۩○◙◙○◙◙○◙◙○◙◙○۩
=>በደቡብ ወሎ በማሻ መቅደላ በርካታ ሙስሊሞች ዳግም እየታሰሩ መሆኑ ተዘገበ
በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ ዚን በማሻ መቅደላ በርካታ ሙስሊሞች መታሰራቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለፍትህ ራዲዬ ገልፀዋል፡፡
በኮማንድ ፖስቱ በሁለተኛው ዙር ቁጥራቸው 17 የሚደርሱ ሙስሊሞች ከዚህ ቀደም ታስረው እንደነበር የሚታወስ ሲሆን እስረኞቹ መፈታታቸው እንደታወቀ ሌሎች ተጨማሪ ወንድሞች ለእስር መዳረጋቸው ተዘግቧል፡፤
የታሰሩት ሙስሊሞች ከቤተሰባቸውም ሆነ ከጠበቆች ጋር እንዳይገናኙ መደረጋቸው የተዘገበ ሲሆን የታሰሩበት ምክንያት እስካሁን አለመታወቁ ተዘግቧል፡፤
17 የሚሆኑት የከተማው ሙስሊሞች ከተንታ ማረሚያ ቤት እና ከብር ሸለቆ የጦር ማሰልጠኛ ተቋም መፈታታቸው የተዘገበ ሲሆን የነሱን መፈታት ተከትሎ ሌሎች በርካታ ሙስሊሞች በወታደሮች ታፍነው መታሰራቸው ታውቋል፡፡
ከታሰሩት ሙስሊሞች መካከል የቀድሞ የወረዳው ሚሊሻ ፅ/ቤት ሀላፊ የነበረው አቶ የሻው እሸቴ፣ አሮ ይማም ሙህዬ፣አቶ መሀመድ ጎንደር እና ሌሎች ስማቸው ያልተጠቀሰ በርካታ ወንድሞች ለእስር መዳረጋቸው ተዘግቧል፡፡
በማሻ ከተማ እስራቱ ቀጥሎ የማሻ ተወላጅ የነበሩ ሁለት ሙስሊም ወንድማማቾች ከደሴ ከተማ ታፍነው መታሰራቸውን የአይን እማኞች ለፍትህ ራዲዬ ባልደረቦች ዘግበዋል፡፡
ሁለቱ ወንድማማች ሙስሊሞች በደሴ ከተማ በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ የነበሩ ሲሆን የመንግስት ሃይሎች ወደ ሱቃቸው በመሄድ በጉልበት እያዳፉ ሁለቱንም ይዘዋቸው እንደሄዱ ለማወቅ ተችሏል፡፤
ሁለቱ ሙስሊሞች ነዋሪነታቸው በደሴ ከተማ ቢሆንም በማሻ ከተማ ከታሰሩት ሙስሊሞች ጋር ንክኪ አላቸው በሚል እንደታሰሩ ተሰምቷል፡:
ሁለቱ ሙስሊም ወንድሞች እስካሁን የታሰሩበት ቦታ አለመታወቁ የተዘገበ ሲሆን በዲናቸው ጠንካራ በመሆናቸው በኮማንድ ፖስቱ ሳይታሰሩ እንዳልቀረ ተዘግቧል፡:
ኮማንድ ፖስቱ ለሁለት ዙር ያህል ንፁሃን ዜጎችን እያፈነ ለእስራት ከዳረገ ቡሃላ ሶስተኛ ዙር የእስር ዘመቻ እንደማይኖር ያስታወቀ ቢሆንም ለሶስተኛ ጊዜ በደቡብ ወሎ ዞን ባሉ ከተሞች ወጣቶች በብዛት እየታፈሱ እንደነበር የአይን እማኞች ለፍትህ ራዲዬ ገልፀዋል፡፡
በደቡብ ወሎ ዞን በሚገኙት በማሻ መቅደላ፣ በሸዋሮቢት፣ከሚሴ፣ ሃርቡ፣ ሃይቅ እና ኮምቦልቻ ከተሞች ወጣቶች ላይ ትኩረት ያደረገ የእስር ዘመቻ እየተካሄደ መሆኑን መዘገባችን ይታወቃል፡፡
በተመሳሳይ በእጅባር ከተማ እና ከኮምቦልቻ ከተማ ስራ ፍለጋ የተሰባሰቡ ወጣቶች በገፍ መታፈሳቸው የተገለፀ ሲሆን በየአቅራቢያው ወደሚገኝ የፖሊስ ማሰልጠኛ ካምፖች መወሰዳቸው ተገልፆል፡፡
በደቡብወሎ ዞን በሚገኙ ወጣቶች ላይ የሚደረገው ጫና ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን የታሳሪ ወጣቶች ወላጅ እናቶች ወጣቶቹ ወደታሰሩበት ቦታ በመሄድ ስለልጆቻቸው ቢጠይቁም ፖሊሶቹ ምላሽ ሳይሰጧቸው እንደቀሩ ታውቋል፡፡
የኮማንድ ፖስቱ የእስር ዘመቻው መቆሙን ቢያስታውቅም በደቡብ ወሎ ዞን ባሉ ከተሞች ግን ለሶስተኛ ጊዜ የእስር ዘመቻ እየተካሄደ ሲሆን በኮምቦልቻ ከተማም ሁለት ባስ መኪና ሙሉ ወጣቶች ታፍሰው በምሽት መወሰዳቸው ን ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወቃል፡፡
በደቡብ ወሎ ዞን በተለይም በዲናቸው ላይ ጠንካራ አንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩ ሙስሊሞች ታፍሰው መታሰራቸውን መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን የተሃድሶ ስልጠና ተሰጥቷቸው ግማሾቹ ከእስር ሲፈቱ ግማሾቹ ጉዳያቸው ወደ ፍርድ ቤት መወሰዱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ተጨማሪ ምስል