በከድር መሐመድ የክስ መዝገብ የተከሰሱት 19 ሙስሊሞች በቀረረባቸው ክስ እንዲከላከሉ ተበየነባቸው

ፍትህ ራዲዬ/ኅዳር 27/2009

۩○◙◙○◙◙○◙◙○◙◙○۩

ከድር መሃመድ የክስ መዝገብ የተከሰሱት ከአዲስ አበባ እና ከጅማ ከተማ በደህንነት ሃይሎች ታፍነው ለእስር የተዳረጉት 19 ሙስሊሞች ለብይን በተሰጣቸው ቀነ ቀጠሮ መሰረት በዛሬው እለት የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት 14ኛ ወንጀል ችሎት መቅረባቸውን የፍትህ ራዲዬ ባልደረቦች ዘግበዋል፡፡

ጋዜጠኛ ዳርሰማ ሶሪ እና ጋዜጠኛ ካሊድ መሀመድን ጨምሮ ቁጥራቸው 19 የሚደርሱት ሙስሊሞች አቃ ህጉ ኢስላማዊ መንግስት ለመመስረት ተንቀሳቅሰዋል፣ ኮሚቴውን በሃይል ለማስፈታት ሞከረዋል እና ህዝብን ለአመፅ ለማነሳሳት በጅማ እና በአዲስ አበባ ከተማ ወረቀት በትነዋል በሚል በሽብር ወንጀል እንደከሰሳቸው የሚታወስ ሲሆን አቃቤ ህጉ የሐሰት ምስክሮቹን ካስደመጠ ቡኋላ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን መርምሮ ውሳኔ ለመስጠጥ ለጀርም ወራት በቀነ ቀጠሮ ሲያንገላታቸው ቆይተዋል፡፡

ተከሳሾቹ በሚቀርቡበት ችሎት ዳኞቹ ገለልተኛ ባለመሆናቸው ዳኞች ይቀየሩልን በሚል አቤቱታ አሰምተው ዳኞች እንደተቀየሩላቸው የሚታወስ ሲሆን በዛሬው ችሎትም ጉዳዩን ሲመለከቱ የነበሩት ዳኞች ተቀይረው የፍርድ ቤቱን ውሳኔ አዲስ ዳኞች እንዳነበቡት ተዘግቧል፡፡

ፍርድ ቤቱም የአቃቤ ህጉን ምስክር በመመርመር በ 19ኙም ተከሳሾች ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ ያስተላለፈ ሲሆን ለቀረበባቸው ክስም እንዲከላከሉ በይኖባቸዋል፡፡

ተከሳሾቹ ለሁለት አመት ገደማ በግፍ በቀነ ቀጠሮ ሲያሰቃያቸው በቆየው ፍርድ ቤት እና በደህንነቶች በሚሾፈረው ችሎት የመከላከያ ምስክሮችን እና ማስረጃዎችን ማቅረብ ጊዜን ማባከን ነው በሚል አንከላከልም ፤ፍርድ ቤቱ የቅጣት ውሳኔውን ያሳውቀን የሚል ምላሽ የሰጡ ሲሆን ፍርድ ቤቱም የተከሳሾችን ምላሽ በመቀበል የቅጣት ውሳኔነውን ለማስተላለፍ ለታህሳስ 4 ቀነ ቀጠሮ መስጠቱን የፍትህ ራዲዬ ባልደረቦች ዘግበዋል፡፡

እነዚህ 19 ሙስሊሞች በተያዙበት ወቅት ጀምሮ ከፍተኛ ድብደባ ይፈፀምባቸው የነበረ ሲሆን በማዕከላዊም ለ5 ወራት ያህል በስቃይ ማሳለፋቸው ይታወሳል፡፡

ከማዕከላዊ ቆይታቸው ቡሃላም መደበኛ የክስ ፋይል ተከፍቶባቸው ወደ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ከተዘዋወሩ ቡኋላ ከፍተኛ በደል እና መከራ ሲያስተናግዱ የቆዩ ሲሆን የቂሊንጦ ማ/ቤት ቃጠሎን ተከትሎም በሸዋሮቢት እና በዝዋይ ማረሚያ ቤት መራራ የግፍ ጊዜን ማሳለፋቸው ይታወቃል፡፡

የመዝገቡ ብቸኛ ሴት ተከሳሽ የነበረችው እህት አያተል ኩብራ በመስከረም ወር በምህረት በሚል ክሷ ተቋርጦ እንድትፈታ መደረጉ የሚታወስ ነው፡፡