በትግራይ ክልል በሼህ አብዱልመናን የክስ መዝገብ የተከሰሱት ሙስሊሞች ከ3አመት እስከ6 ወር የሚደርስ እስራት ቅጣት ተበየነባቸው
ፍትህ ራዲዬ/ ሐምሌ 6/2009
۩○◙◙○◙◙○◙◙○◙◙○۩
በትግራይ ክልል በደቡባዊ ዞን በራያ አዘቦ ዋሃቢያ ናችሁ በሚል ለእስር የተዳረጉት በሼህ አብዱልመናን የክስ መዝገብ የተከሰሱት ኡለሞች እና ኡስታዞች በቀነ ቀሯቸው መሰረት ሰኔ 17/2009 ፍርድ ቤት ለብይን ቀርበው እንደነበር የፍትህ ራዲዬ በልደረቦች ዘግበዋል፡፡
በግንቦት 25 በነበራቸው ችሎት ተከሳሾቹ የቀረበባቸውን የሽብር ክስ በመሰረዝ መንግስትን በመሳደብ በሚል እንዲቀየር መወሰኑ ይታወቃል፡፡
አቃቤ ህጉ ለሽብር ክሱ ያስረዱልኛል ያላቸውን ምስክሮች ለፍርድ ቤቱ አስደምጦ እንደነበር መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን ከምስክሮችም መካከል ሸኽ ኣብድልመናን 2006 ላይ በሳዉዲ ኣረብያ ረያድ መንፉሓ በተባለ ቦታ መስጂድ ላይ ኢትዮጵያ ዉስጥ መንግስት ሙስሊም ወንድሞቻችን(እነ ኡስታዝ ያሲን ኑሩን) ስላሰረ ለቤተሰቦቻቸዉ የሚሆን እርዳታ እናድርግ ማለታቸዉ ለመንግስት ፖሊሲ ያላቸዉ ጥላቻ ያመላክታል የሚል የምስክር ቃል የሰጡ መኖራቸው ይታወሳል፡፡
ቀሪ ምስክሮች ባጠቃላይ ምንጩ ባልታወቀ ገንዘብ መስጂዶችን ያሰሩ ነበር፣ ብርድ ልብሶች ለደካሞች ያድሉ ነበር፣ ዱቄት ያከፋፍሉ ነበር ፣ቧምቧ ውሃ ያስሩ ነበር በማለት የምስክር ቃላቸውን መስጠታቸው ይታወሳል፡፡
ፍርድ ቤቱ የሁሉንም ምስክሮች ቃል ካደመጠ ቡሃላ አቃቤ ህጉ ያቀረበው የሽብር ክስ ውድቅ እንዲሆን እና በመደበኛ የወንጀል ህግ መንግስትን በመሳደብ በሚል ወንጀል እንዲከላከሉ ውሳኔ እንዳስተላለባቸው ይታወቃል፡፡
ተከሳሾቹ መከላከያ ምስክሮቻቸውን ለፍርድ ቤቱ ቢያቀርቡም ሁለት ተከሳሾችን በነፃ እንዲሰናበቱ ሲበይን በቀረዎቹ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ ማስተላለፉ ተዘግቧል፡፡
ሼህ ናስር እና አቶ አህመድ ግደይ ከቀረበባቸው ክስ ነፃ በሚል በነፃ እንዲለቀቁ ፍርድ ቤቱ የበየነላቸው ሲሆን ቀሪዎቹ ግን ጥፋተኛ ናቸው በሚል የጥፋተኝነት ብይን እንደተላለፈባቸው ታውቋል፡፡
ሼህ አብዱልመናን በቀረበባቸው ክስ 3መት ከ6ወራት እስራት ቅጣት ሲበየንባቸው በሳቸው ክስ የነበሩት ሼህ አህመድ ዩሱፍ፣ሼህ ከድር ሀሰን አቶ አህመድ ሱለይማን እና ሌሎች 3 ሙስሊሞች እያንዳንዳቸው የ 1 አመት ከ 6 ወራት እስራት እንደተበየነባቸው የፍትህ ራዲዬ ባልደረቦች ዘግበዋል፡፡
የ 1 አመት ከ 6 ወራት የተበየነባቸው ሙስሊሞች የእስራት ጊዜያቸው የተጠናቀቀ በመሆኑ በቅርቡ እንደሚፈቱ የታወቀ ሲሆን ሼህ አብዱልመናን ግን ቀሪ የእስር ጊዜያቸውን ማጠናቀቅ እንደሚኖርባቸው ተገልፆል፡፡

ተጨማሪ ምስል