በትግራይ ክልል በራያ አዘቦ ወረዳ የታሰሩት ኡለሞች እና ኡስታዞች ፍ/ቤት ሳይቀርቡ ለጥር 18 ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጣቸው

ፍትህ ራዲዬ/ታህሳስ 18/2009

۩○◙◙○◙◙○◙◙○◙◙○۩

በትግራይ ክልል በደቡባዊ ዞን በራያ አዘቦ ዋሃቢያ ናችሁ በሚል ለእስር የተዳረጉት ኡለሞች እና ኡስታዞች ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ቀነ ቀጠሯቸው ወደ ጥር 18 እንዲዘዋወር መደረጉን የፍትህ ራዲዬ ባልደረቦች ዘግበዋል፡፡

ኡለሞቹ እና ኡስታዞቹ በራያ አዘቦ ወረዳ ኩኩፍቶ በተባለ ቦታ የተያዙ ሲሆን ማይጨው በሚገኘው ማዕከላዊ እስር ቤት ታስረው እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡

ከታሰሩት ኡለሞች እና ኡስታዞች መካከል ከሳኡዲ አረቢያ ለቤተሰብ ጥየቃ ወደ ሃገራቸው የተመለሱት ኡስታዝ አብዱልመናንን ጨምሮ በአፍሪካ ቲቪ የትግርኛ ዳዕዋ በማድረግ የሚታወቀው ኡስታዝ ከድር ሁሴን፣ሼህ አህመድ ዩሱፍ እና ሌሎችም ሙስሊሞች በግፍ ታስረው እየተሰቃዩ መሆኑን የፍትህ ራዲዬ መዘገቧ ይታወሳል፡፡

አቃቤ ህጉ ካቀረበባቸው ክስ መካከል ቅሬ(እድር) ላይ አትሳተፉም፣ ዋሃቢያ ናችሁ፣ አብደላህ አል ሃረሪን አትቀበሉም፣ልጆች መልምላችሁ ወደ ሳኡዲ አረቢያ ትልካላችሁ የሚሉን አሳፋሪ የሃሰት ክሶች እንደሚገኙበት መዘገባችን ይታወሳል፡፡

በቀረበባች ሃሰተኛ ክስ ላይም አቃቤ ህጉ አሉኝ ያለቸውን ምስክሮቹን ለፍርድ ቤት እንዲያቀርብ ትዕዛዝ መሰጠቱ የሚታወስ ሲሆን ከቀነ ቀጠሮ በፊት ታህሳስ 11 ቀን ቀነ ቀጠሯቸው ወደ ጥር 18 መዘዋወሩን የሚገልፅ ማስታወቂያ መለጠፋቸው ተዘግቧል፡፡

የመንግስት አቃቤ ህግ የሆነው አቶ ኢድሪስ ጀማል የሃሰት ምስክሮቹን ለማቅረብ በመቸገሩ ከዳኞቹ ጋር በመነጋገር ተከሳሾችም ሆኑ ጠበቆቻቸው ባልተገኙበት ቀነ ቀጠሮው ወደ ጥር 18 እንዲዘዋወር መደረጉን የሚገልፅ ብጣሽ ወረቀት በፍርድ ቤቱ ማስታወቂያ ቦርድ ላይ ማስለጠፉ ታውቋል፡፡

ቀነ ቀጠሮውን ያለህግ አግባብ እንዲዘዋወር በመደረጉ የታሳሪ ቤተሰቦች ቅሬታቸውን ወደመቀሌ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በመሄድ ማቅረባቸው ተዘግቧል፡፡

የመቀሌ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት የሆነው አቶ ዘነበ አቤቱታውን ባቀረቡት ቤተሰቦች ላይ ከፍተኛ ማስፈራሪያ እና ዛቻ እንደፈፀመበቸው የፍትህ ራዲዬ ባልደረቦች ዘግበዋል፡፡

አቶ ዘነበ ለተከሳሽ ቤተሰቦች ይህ ጉዳይ በቀጥታ እኔ እና የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳደሩ አቶ አባይ ወልዱ በቅርበት እየተከታተልነው ነው፡፡ ዳግመኛ እንዲህ አይነት ጥያቄ ብታቀርቡ ለእስር እንደምትዳረጉ ማወቅ አለባችሁ፡፡ ሁላችሁንም መልካችሁን በደንብ ተመልክቻለው፡፡ምንም አይነት ነገር ቢፈጠር ለወረዳው ፖሊስ በማሳወቅ አሳስራቹሃለው በማለት የታሳሪ ቤተሰቦችን ማስፈራራቱ ተዘግቧል፡፡

በሼህ አብዱልመናን መዝገብ የተከሰሱት እነዚህ ሙስሊሞች ያለበቂ መስረጃ ለእስራ ከተዳረጉ ድፍን አንድ አመት ሊሞላቸው መሆኑ የተገለጸ ሲሆን በሐሰት ተወንጅለው በቀነ ቀጠሮ በማረሚያ ቤት እየተሰቃዩ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡

ተጨማሪ ምስል