በትግራይ ክልል በራያ አዘቦ ወረዳ የታሰሩት ኡለሞች እና ኡስታዞች አቃቤ ህጉ ተጨማሪ የሰነድ እና የሰው ምስክሮችን ለመጋቢት 11 እንዲያቀርብ በሚል ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጣቸው

ፍትህ ራዲዬ/ የካቲት 15/2009
۩○◙◙○◙◙○◙◙○◙◙○۩

በትግራይ ክልል በደቡባዊ ዞን በራያ አዘቦ ዋሃቢያ ናችሁ በሚል ለእስር የተዳረጉት በሼህ አብዱልመናን የክስ መዝገብ የተከሰሱት ኡለሞች እና ኡስታዞች በቀነ ቀሯቸው መሰረት የካቲት 13 ፍርድ ቤት መቅረባቸውን የፍትህ ራዲዬ ባልደረቦች ዘግበዋል፡፡

ኡለሞቹ እና ኡስታዞቹ በራያ አዘቦ ወረዳ ኩኩፍቶ በተባለ ቦታ የተያዙ ሲሆን ማይጨው በሚገኘው ማዕከላዊ እስር ቤት ታስረው እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡

ከታሰሩት ኡለሞች እና ኡስታዞች መካከል ከሳኡዲ አረቢያ ለቤተሰብ ጥየቃ ወደ ሃገራቸው የተመለሱት ኡስታዝ አብዱልመናንን ጨምሮ በአፍሪካ ቲቪ የትግርኛ ዳዕዋ በማድረግ የሚታወቀው ኡስታዝ ከድር ሁሴን፣ሼህ አህመድ ዩሱፍ እና ሌሎችም ሙስሊሞች በግፍ ታስረው እየተሰቃዩ መሆኑን የፍትህ ራዲዬ መዘገቧ ይታወሳል፡፡

አቃቤ ህጉ ካቀረበባቸው ክስ መካከል ቅሬ(እድር) ላይ አትሳተፉም፣ ዋሃቢያ ናችሁ፣ አብደላህ አል ሃረሪን አትቀበሉም፣ልጆች መልምላችሁ ወደ ሳኡዲ አረቢያ ትልካላችሁ የሚሉን አሳፋሪ የሃሰት ክሶች እንደሚገኙበት መዘገባችን ይታወሳል፡፡

የመንግስት አቃቤ ህግ የሆነው አቶ ኢድሪስ ጀማል የሃሰት ምስክሮቹን ለማቅረብ በመቸገሩ ከዳኞቹ ጋር በመነጋገር ቀነ ቀጠሮውን ሲያራዝም መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን በሁኔታው ያዘኑት የታሳሪ ቤተሰቦች ቅሬታቸውን ወደመቀሌ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በመሄድ ቢያቀርቡም የመቀሌ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት የሆነው አቶ ዘነበ አቤቱታውን ባቀረቡት ቤተሰቦች ላይ ከፍተኛ ማስፈራሪያ እና ዛቻ እንደፈፀመበቸው መዘገባችን ይታወሳል ፡፡

በሼህ አብዱልመናን መዝገብ የተከሰሱት እነዚህ ሙስሊሞች በቀነ ቀጠሯቸው መሰረት የካቲት 13 ፍርድ ቤት ቀርበው የነበረ ሲሆን ጉዳያቸውን እየተመለከቱት የሚገኙት የፍርድ ቤቱ ዳኞች እና አቃቤ ህጉ የሽብር ክስ ለመመርመር ብቁ ኣይደላችሁም፣ የፌደራል ጸረ ሽብር ስልጠና አልወሰዳችሁም በመሆኑም ይህን ጉዳይ ለመመርመር ብቁ መሆናችሁን የሚያረጋግጥ ሴርትፍከት ካላችሁ ኣቅርቡ የሚል ጥያቄ በተከሳሽ ጠበቆች በኩል በቀረበላቸው መሰረት ኣቃብ ህግ ሽብርን ለመመርመር እና ለመክሰስ ያስችለኛል ያለዉ ማስረጃ ከፈድራል ፖሊስ ጸረ- ሽብር ግብረ ሃይል በማምጣት ለችሎቱ ማቅረቡ ተዘግቧል፡፡

በቀረበው ማስረጃ ላይም የተከሳሽ ጠበቃ በበኩሉ የቀረበው ማስረጃ ወንጅልን መከላከል እና መቆጣጠር ይችላል የሚል እንጂ ስለሽብር የወሰደዉ ስልጠና ስለመኖሩ የሚገልፅ ስርተፍኬት አላቀረበም በሚል ተቃውሞውን አሰምቷል፡፤

ፍርድ ቤቱም በአቃቤ ህጉ በኩል ለቀረበው ክስ የሚያጠናክሩለትን ተጨማሪ የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎች ለመጋቢት 11 ይዞ እንዲቀርብ ቀነ ቀጠሮ በመስጠት ችሎቱ መጠናቀቁን የፍትህ ራዲዬ ባልደረቦች ዘግበዋል፡፡

ተጨማሪ ምስል