በቢሾፍቱ በሰላማዊ ዜጎቻችን ላይ መንግስት የወሰደውን ኃላፊነት የጎደለውን  አረመኔያዊ እርምጃ  በጽኑ እንደሚያወግዝ ድምፃችን ይሰማ አስታወቀ

ፍትህ ራዲዬ/መስከረም 25/2009
۩○◙◙○◙◙○◙◙○◙◙○۩

መንግስት  የኢሬቻ በአልን ለማክበር በተሰበሰቡ በሚሊዬን በሚቆጠሩ ዜጎች ላይ የወሰደውን የሃይል እርምጃ እና እልቂት ድምፃችን ይሰማ እንደሚያወግዘው ዛሬ መስከረም 15/2009 ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

ከመንግስት በርካታ ኃላፊነቶች መካከል የአገርን ህልውና እና የህዝብን ሰላም ማስጠበቅ ቀዳሚዎቹ ቢሆንም  በአገራችን ያለው ግን ከዚህ በተቃራኒ ሆኖ  በሚያሳዝን መልኩ በአገራችን እየተከሰቱ ያሉ ሰላም የሚያደፈርሱና ህልውናችንን አደጋ ላይ የሚጥሉ ክስተቶች በአብዛኛው ምንጫቸው መንግስት ሆኖ እንደሚገኝ ድምፃችን ይሰማ አስታውቋልል፡፡

ከሰሞኑም ኃላፊነት በጎደለው የመንግስት እርምጃ በርካታ ዜጎቻችን በአሰቃቂ ሁኔታ ለሞት መዳረጋቸውን ድምፃችን ይሰማ የገለፀ ሲሆን  ይህ ድርጊት በየትኛውም መመዘኛ በጽኑው የሚወገዝ  እና  ስርዓቱ ምንግዜም ከስህተቱ የማይማር፣ ሰላማዊ ጥያቄን ከሚያነሱ ዜጎች ጋር ለመግባባት ከኃይል እና አፈሙዝ ውጭ ሌላ ቋንቋ እንደሌለው በግልጽ የሚያሳይ መሆኑን ድምፃችን ይሰማ በመግለጫው አስታውቋል፡፡

ከሰሞኑ በቢሾፍቱ (ደብረ ዘይት) የተፈጠረው አሳዛኝ ክስተት ማቆሚያ ያልተበጀለት የመንግስታዊው ጥቁር ሽብር ውጤት ነው  ሲል ድምፃችን ይሰማ ያስታወቀ ሲሆን  ይህ ክስተት በአገራችን ታሪክ በህዝብ ላይ የማይሽር ጠባሳ ጥለው ካለፉ አሳዛኝ ክስተቶች መካከል አንዱ ሆኖ ዘወትር ሊታወስ በታሪክ ተመዝግቧል ብሏል፡፡

በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በአፋር እና በሶማሊያ ክልሎች ላለፉት አምስት ዓመታት በመላው ሙስሊሙ ህብረተሰብ ላይ እየደረሰ ያለው የመብት ረገጣ እና የሰላማዊ ዜጎች ህልፈት ትምህርት አልሆን ብሎ ዛሬም ዘግናኝ የመንግስት አረመኔያዊ እርምጃዎች ቀጥለው እያየን ነው ያለ ሲሆን  መንግስት አሁንም ድረስ ውስጡን ከመፈተሽ ይልቅ ህዝብ የሚያውቀውን እውነታ በማድበስበስ እጁን ወደሌሎች ለመቀሰር መሞከሩ በህዝብ ዘንድ የማይበርድ ቁጭት የሚፈጥር ኃላፊነት የጎደለው ተግባር መሆኑ እንደማያጠራጥር ድምፃችን ይሰማ አስታውቋል፡፡

ከዚህ አሳዛኝ ክስተት ማግስት ከህዝብ ተነጥቀው የስርዓቱ የፕሮፓጋንዳ ማራመጃ በተደረጉ የህዝብ ሚዲያዎች የሚሰነዘሩት ሃሳቦች ሐዘን ባቆሰለው ህዝብ ላይ ሌላ ድርብ ህመም የሚፈጥሩ ናቸው ያለ ሲሆን  ይህ ግን የመታገልን ስሜት የሚገነባ እንጂ የፍርሃት ድባብን በፍፁም አያነግስም ሲል ድምፃችን ይሰማ በመግለጫው አስታውሷል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝቦች የቱንም ያክል ድምጻቸውን ከፍ አድርገው እና ደጋግመው ቢያሰሙም የስርዓቱ ተደጋጋሚ መልስ የሚወስዳቸውን የሃይል እርምጃ ከማጠናከር ውጭ ሌላ ሊሆን አልቻለም። በዚህ መልኩ የሚኖረው እድሜ ረጅም ሊሆን አይችልም። በዚህ ነባራዊ ሁኔታ በህዝቦች መካከል ያለውን አንድነት፣ ትብብር እና እርስ በርስ መግባባት ማጠናከር እንዳለ ሆኖ ህዝቦች በቀጣይ እንድትኖራቸው በሚፈልጓት ኢትዮጵያ ዙሪያ በሰፊው ሊመክሩ እንደሚገባ  ድምፃችን ይሰማ አሳስቧል፡፡

ድምፃችን ይሰማ ኃላፊነት የጎደለውን የመንግስት አረመኔያዊ ድርጊት አጥብቀን እናወግዛለን ያለ ሲሆን  በሰላማዊ ወገኖቻችን ላይ በደረሰው እልቂት የተሰማንን መሪር ሐዘን እየገለፅን ለተጎጂ ቤተሰቦች እና ለመላው ኢትዮጵያውያንም መፅናናትን እንመኛለን በማለት መግለጫውን አጠናቋል፡፡