በሸዋሮቢት በግፍ ታስር የሚገኙት እስረኞች ቤተሰቦች ለአንድ ሳምንት ወደ ማረሚያ ቤቱ እንዳይመጡ እንደተነገራቸው ተዘገበ ፍትህ ራዲዬ/ጥቅምት 9/2009 ۩○◙◙○◙◙○◙◙○◙◙○۩ በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የተነሳውን እሳት ቃጠሎ ተከትሎ ወደ ሸዋሮቢት እንዲዘዋወሩ ከተደረጉት እስረኞች መካከል በሸዋሮቢት እንዲታሰሩ የተደረጉት ሙስሊሞች ቤተሰቦቻቸው ለአንድ ሳምንት ወደ ማረሚያ ቤቱ እንዳይመጡ እንደተከለከሉ የፍትህ ራዲዬ ባልደረቦች ዘግበዋል፡፡ በማረሚያ ቤቱ ከፍተኛ በደል እና ስቃይ እየተፈፀመባቸው መሆኑን መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን በሚፈፀምባቸው ድብደባ እና ስቃይም መራመድ እንዳቃታቸው ቤተሰቦቻቸው ለፍትህ ራዲዬ ገልፀዋል፡፡ በጥቅምት 6/2009 ወደ ሸዋሮቢት የተጓዙት የነዚህ ሙስሊም እስረኞች ቤተሰቦች ለአንድ ሳምንት ያህል ወደ ማረሚያ ቤቱ ተመልሰው እንዳይመጡ የተነገራቸው ሲሆን ቢመጡም ከታሳሪዎች ጋር እንደማያገናኟቸው እንደገለፁላቸው ታውቋል፡፡ ምክንያቱ በግልፅ ባልተቀመጠበት ሁኔታ ለምን አትምጡ ተባልን በማለት ወላጅ እናቶች ወደ ማረሚያ ቤቱ ምግብ ይዘው ቢሄዱም ከልጆቻቸው እና ከቤተሰባቸው ጋር መገናኘት እንዳልቻሉ ተዘግቧል፡፡ ለቤተሰባቸው ይዘውት የሄዱት ምግብም አይገባም ተብሎ የተመለሰባቸው ሲሆን ለ 1 ሳምንት ቆይታችሁ ተመልሳችሁ ኑ የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ታውቋል፡፡ በሸዋሮቢት የታሰሩት እስረኞች አካላቸው ተጎሳቁሎ፣መራመድ አቅቷቸው ከፍተኛ ጉዳት ላይ እንደሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ለፍትህ ራዲዬ የገለፁ ሲሆን አሁን ደግሞ ለ 1 ሳምንት እንዳትመጡ መባላቸው ምን ተፈጥሮ ይሆን በሚል ጭንቀት ውስጥ መውደቃቸው ተዘግቧል፡፡ በተያያዘ ዜናም በጥቅምት 2/2009 ከዝዋይ ማረሚያ ቤት ወደ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የተመለሱት ቁጥራቸው ወደ 300 የሚጠጉ እስረኞች ከቤተሰቦቸው ጋር ለ 3 ደቂቃ ብቻ እንዲገናኙ እንደተፈቀደላቸው የፍትህ ራዲዬ ባልደረቦች ዘግበዋል፡፡ ከዝዋይ ማረሚያ ቤት የተመለሱትን እነዚህ እስረኞች በዞን ሁለት ውስጥ በልዩ ጥበቃ ስር እንዲታሰሩ መደረጉ የታወቀ ሲሆን የቤተሰብ መጠየቂያ ሰአቱ በመደበኛው ሙሉ ቀን ቢሆንም ከቤተሰቦቻቸው ጋር ግን ለ 3 ደቂቃ ብቻ እንዲገናኙ እየተደረገ መሆኑ ታውቋል፡፡ ከቤተሰቦቻቸውም ጋር ሲገናኙ ከሰላምታ ውጪ ሌላ ነገር መነጋገር የማፈቀድላቸው ሲሆን በሶስት ደቂቃ ውስጥ ብቻ ተገናኝተው እንደሚለያዩ ተዘግቧል፡፡