መንግስት የህዝቡን ተቃውሞ ከአቅም በላይ ስለሆነበት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጀ

ፍትህ ራዲዬ/መስከረም 29/2009
۩○◙◙○◙◙○◙◙○◙◙○۩

የኢትዬጲያ መንግስት ባለፈው ሳምንት የኢሬቻ በዓልን ለማክበር በወጡ በሚሊዬን በሚቆጠሩ ዜጎች ላይ    በወሰደው የሃይል እርምጃ በርካቶች ህይወታቸውን ማለፉን ተከትሎ ከባድ ቁጣ በህዝቡ በመቀስቀሱ በኦሮሚያ ክልል በሰፈነው ከባድ ተቃውሞ የተነሳ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን ሃይለማርያም ደሳለኝ በዛሬው እለት ማስታወቁ ተዘግቧል፡፡

 የሀገሪቱን ሰላም የማይሹ ኃይሎች ከውጭ ጠላቶች ጋር በማበር በሀገሪቱ ህዝብ ሰላም፣ ፀጥታና ደህንነት ላይ የደቀኑትን ከፍተኛ ስጋት ለመቀልበስ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከትንናንት ጀምሮ የሚተገበር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ በይፋ ለህዝቡ በሚዲያ ያስታወቁ ሲሆን የዚህ መሰሉ አስኳይ ጊዜ አዋጅ ሲታወጅ በ 25 አመት ውስጥ የመጀመሪያው ነው ተብሏል፡፡

መንግስት በህዝቡ ዘንድ የገጠመው ከባድ ተቃውሞ ብዙሃኑን ቢጨፈጭፍም ሊቆም ባለመቻሉ ተጨማሪ የሃይል እርምጃዎችን ለመውሰድ ያመቸው ዘንድ ያስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጀ ሲሆን   ይህ ያስቸኳይ ጊዜም ለ 6 ወራት የሚቆይ መሆኑ ተገልፆል፡፡

በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ የገበሬውን መሬት ነጥቀው ፋብሪካ የገነቡ እና የመንግስት ንብረቶች መውደማቸው የሚታወቅ ሲሆን ይህን የህዝቡን ቁጣም የውጪ ሃይሎች ተግባር ነው በሚል በመንግስት ፕሮፖጋንዳ እየተሰራ መሆኑ ተዘግቧል፡፡

ተቃውሞ በሚካሄድባቸው ቦታዎች ሁልጊዜም ያስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እየታወጀ ህዝቡን ሲያስሩ እና ሲደበድቡ እንደነበር የታወቀ ሲሆን በመላው ሃገሪቱ ተቃውሞ እንዳይባባስ በመስጋት ያሁኑ ሃገር አቀፍ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጃቸው ታውቋል፡፡

በአንድ ሳምንት ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ንፁሀን ዜጎች በወታደሮች መገደላቸው የሚታወቅ ሲሆን ከወታደሮችም በኩል በርካቶች መሞታቸው ተዘግቧል፡፡