እኛም እስከመጨረሻው በፅናት ከመታገል ውጭ ሌላ አቋራጭ መንገገድ የለንም! 
ሐሙስ ሐምሌ 28/2008

ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች መንግስት መራሹን ሃይማኖታዊ ጣልቃ ገብነት ስንታገል ይኸው ዓመታትን አሳልፈናል፡፡ በዚህ ወቅት ሁሉ መብታችንን በዘላቂነት ለማስከበር በጽናት የቆምን ሲሆን በሂደትም ዘርፈ ብዙ ልምድን፣ ጠንካራ የእምነት ትስስርን እና መደጋገፍን መሠረት ያደረገ ወንድማማችነት መመስረት ችለናል። በዚህም እኛን ለመከፋፈል የተደረጉ የመንግስትን በርካታ ሴራዎች ለማምከን ችለናል - አልሐምዱሊላህ! በመንግስት ጋሻ ጃግሬነት እየተካሄደ ያለውን የብሄራዊ ጭቆና ዘመቻ ጸንተን ከመታገል ውጭ ሌላ አቋራጭ መንገድ አለመኖሩን በትግላችን ሂደት ለመረዳትም ችለናል፡፡ መንግስት በእብሪተኝነቱ መቀጠሉ እና የህዝብን ድምጽ ከምንም ባለመቁጠር በአምባገነንነት ጭቆናውን አጠናክሮ መቀጠሉ ይህንን እውነታ ያጠናክራል።

ሙስሊሙ ህብረተሰብ መንግስታዊውን ህገወጥ የሃይማኖት ጣልቃ ገብነት ተቃውሞ ያነሳቸው ጥያቄዎች ሙሉ በሙሉ ህጋዊ እና ፍትሃዊ ሲሆኑ ጥያቄዎቻችን ይመለሱ ዘንድ የተጓዝንበት የትግል ጎዳናም እጅግ ሰላማዊ ነው። ምንም እንኳን ለፍትሃዊ ጥያቄዎቻችን እና ለሰላማዊ ሂደታችን ከመንግስት ያገኘነው መልስ በኢሰብአዊነት የተሞላ እና ህግን የጣሰ ሆኖ ቢቀጥልም እስካሁንም ድረስ ግን ህዝበ ሙስሊሙ ከሰላማዊነት መርሁ አንዳችም ፈቀቅ ሳይል የትግል ሂደቱን ማእቀፍ በማጠናከር እና በማስፋት በትግሉ እንደቀጠለ ይገኛል፡፡

ከሕዝበ ሙስሊሙ ትግል ጎን ለጎን መንግስት ለሙስሊሙ ጥያቄ እልባት ይሰጥ ዘንድ አገር ወዳድ አባቶች በሽምግልና ሂደት ብዙ እልህ እስጨራሽ ሂደቶችን ሲጓዙ ቆይተዋል፡፡ ከእስር የተፈቱ ወንድሞች እና አባቶችም ለዚህ ሂደት ጉልበት በመሆን የተለያዩ ጥረቶችን እያደረጉ ቢቆዩም ወትሮም መፍትሄ ለማፈላለግ በህዝብ የተላኩ የሰላም አምባሳደሮችን በአሸባሪነት ፈርጆ እያሰቃየ ያለው ስርአት ግን በሙስሊሙ ላይ እያደረሰ ያለውን በደል አስፍቶ እና አጠናክሮ መቀጠልን መርጧል። በሙስሊሙ ሃይማኖታዊ እና የዜግነት መብት ላይ ያወጀው ብሄራዊ ጭቆና ሳያንሰው በግለሰቦች ላይ ሳይቀር የፕሮፓጋንዳ ጦርነት ለመክፈት መምረጡ በራሱ ለብዙዎች ልዩ መልዕክትን የሚያስተላልፍ ነው። እነዚህ ሁሉ መንግስት ሙስሊሙን ህብረተሰብ እንደ ማህበረሰብም እንደ ግለሰብም ድርብርብ ጭቆና ውስጥ ለማስቀመጥ እያደገ ያለውን ጥረት ፍንትው አድርገው የሚያሳዩ ናቸው። የአህባሽን አስተምህሮት በሙስሊሙ ህብረተሰብ ላይ የመጫን ፕሮጀክትም በተጠናከረ መልኩ የማስቀጠል እንቅስቃሴዎችን እያደረገ መሆኑም ሙስሊሙ ህብረተሰብ ለእምነቱ እና ለመብቱ በጽናት ከመቆም ሌላ አማራጭ እንደሌለው አስረጅ ነው።

መንግስት በኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ላይ ያወጀው ብሄራዊ ጭቆና ዓይን ላለው እና ማሰብ ለሚችል ሁሉ ግልጽ ነው፡፡ ሙስሊሙ ህበረተሰብ ይህንን እውነታ ገና ከጠዋቱ የተረዳው ቢሆንም አማራጭ መንገዶች ካሉ በማለት ከላይ እንደጠቀስነው የሽምግልና ሂደት ውስጥ ገብተው የራሳቸውን ጥረት ቢያደርጉም እምቢተኛው ስርዓት ግን ይህን እድል እንኳን ለመጠቀም ፈቃደኛ አልሆነም። ይህንን የተረዳ ህብረተሰብ ደግሞ ራሱን ለረጅም ትግል አዘጋጅቶ በፅናት ከመታገል ውጭ ሌላ አቋራጭ መንገድ አለመኖሩንም ይረዳል።

ምንም እንኳን ሰላማዊ የትግል መርሃችንን እና ሰላማዊ መፍትሄ መሻታችንን አምባገነኑ ስርዓት እንደ ድክመት ቢያየውም ሰላማዊ የትግል ሂደታችን እና እያንዳንዱ የተጓዝንባቸው ውስብስብ ጥረቶች የዘላቂ ድላችን ዋስትና ሆነው ይቀጥላሉ። ከሰላማዊ የትግል መርሃችን ሳንዛነፍ ትግላችንን አጠንክረን እንቀጥላለን፤ ትግላችንም በአላህ ፈቃድ በድል እንደሚቋጭ ምንም ጥርጥር የለውም!

ራሳችንን ለረጅም ትግል አዘጋጅተን በፅናት ከመታገል ውጭ ሌላ አቋራጭ መንገድ የለንም!
ትግላችን እስከድል ደጃፎች በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል!
ድምጻችን ይሰማል!
አላሁ አክበር!

Like ☑ Comment ☑ Share ☑